ቀጥታ፡

የዳያስፖራው ድጋፍ ለመከላከያ ሠራዊቱ የሞራል ስንቅ ሆኖታል

ጥቅምት 19 ቀን 2014 (ኢዜአ) "ዳያስፖራው እያደረገ ያለው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ለመከላከያ ሠራዊቱ የሞራል ስንቅ እየሆነው ነው'' ሲሉ የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ምክትል አዛዥ ብርጋዴር ጄነራል ሙሉዓለም አድማሱ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት በህልውና ዘመቻው ተጎድተው በሰሜን ምዕራብ ዕዝ ሆስፒታል ህክምና ላይ ለሚገኙ የሠራዊት አባላት ዛሬ የአልባሳት ድጋፍ አድርጓል።

በድጋፍ አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ብርጋዴር ጄነራል ሙሉዓለም አድማሱ እንዳሉት፤ አሸባሪው ህወሓት አገር የማፍረስ ግብ ይዞ በአማራና አፋር ክልሎች የፈጸመው ወረራ ከሽፎበታል።

መንግስት፣ ህዝብ፣ መከላከያ ሠራዊቱና ሌሎች የጸጥታ ሀይሎች በጽናት በመታገል የአሸባሪውን ቅዠት ከንቱ እንዳደረጉበት ተናግረዋል።

የአሸባሪውን ህወሓት አገር የማፍረስ ተልዕኮ በሚገባ በመመከት ሰላሟ የተረጋገጠ ኢትዮጵያ እንድትኖር መከላከያ ሠራዊቱ እየከፈለ ላለው መስዋዕትነት የህዝቡ ድጋፍ ከፍተኛ ሞራል መሆኑንም ገልጸዋል።

መስዋዕትነት ለከፈሉ የመከላከያ ሠራዊት አባላት የዳያስፖራው ማህበረሰብ አጋርነቱን ማሳያቱ ደግሞ ከድጋፍ ባለፈ የሞራል ስንቅነቱ ከፍተኛ መሆኑን ነው የተናገሩት።

"ኢትዮጵያ የጀግኖች ሀገር በመሆኗ አትበተንም፤ ተከብራ ስለኖረች ወደፊትም ክብሯ እንደተጠበቀ ትኖራለች" ሲሉ ብርጋዴር ጄነራሉ አክለዋል።

"መከላከያ ሠራዊቱ ድል የሚያስመዘግበው ከህዝቡ ጋር በመሆኑ በርቱ፣ ጠንክሩ የሚለው ድጋፍ   መቀጠል ይኖርበታል" ሲሉም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት ሊቀመንበር አቶ ዓለማየሁ አበበ በበኩላቸው ያሉትን ችግሮች በመለየት የዳያስፖራው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በሰሜን ምዕራብ ዕዝ የመከላከያ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው ለሚገኙ የሠራዊቱ አባላት 500 ቲሸርት፣ 500 ነጠላ ጫማ፣ 500 ቁምጣና የምግብ ማቀዝቀዣ ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም