ቀጥታ፡

በአገር ውስጥ የኤፍ ኤም ጣቢያዎች የውጭ አገር ፕሮግራሞችን ሊንክ አድርጎ ማስተላለፍ ተከለከለ

ጥቅምት 19 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአገር ውስጥ የኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች የውጭ አገር ፕሮግራሞችን ሊንክ አድርጎ ማስተላለፍ ከዛሬ ጀምሮ መከልከሉን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

በአገር ውስጥ ፈቃድ ያልተሰጣቸው የውጭ አገር የሬዲዮ ጣቢያዎች ፈቃድ ባላቸው የአገር ውስጥ የኤፍ ኤም ማሰራጫ ጣቢያዎች አማካኝነት ፕሮግራሞቻቸውን ሲያስተላልፉ መቆየታቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሃመድ እድሪስ በተለይ ለኢዜአ በሰጡት መግለጫ በአገር ውስጥ የኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች የውጭ አገር ፕሮግራሞችን ሊንክ አድርጎ ማስተላላፍ ከዛሬ ጀምሮ ተከልክሏል።

በውጭ አገራት የሚሰሩ የሬዲዮ ጣቢያዎች የሚተላለፉ ፕሮግራሞች የአገር ውስጥ ህግና ስርዓትን ተከትለው አይካሄዱም፡፡

"በፕሮግራሞቹ የአንዳንድ አገራት አቋም መግለጫ ሲተለለፍ የሚታይበት እና የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ግምት ውስጥ ያላስገ ሲሆን ተስተውሏል" ብለዋል።

በተጨማሪም የአገሪቷን ፖለቲካዊ ነበራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያላስገቡ ፕሮግራሞችም ሲተላላፉ እንደነበርም አስታውሰዋል።

እነዚህ አካላት በአገር ውስጥ ፈቃድ ያላገኙ በመሆናቸው የሚተላለፉ መርሃ ግብሮችን በመከታተል ግብረ መልስና የማስተካከያ ሃሳብ ለመስጠት የሚቻልበት ሁኔታ አለመኖሩንም ገልጸዋል፡፡   

በአገር ውስጥ የሚያስተላልፉ የኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎችም ፕሮግራሞቹ ላይ የሚያደርጉት ቁጥጥር አነስተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

የተጠቀሱትን ሃሳቦች ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ባለስልጣኑ ከዛሬ ጀምሮ ከውጭ ሚዲያዎች ወደ አገር ውስጥ የኤፍ ኤም ጣቢያዎች ሊንክ አድርጎ ማስተላለፍን ከልክሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም