የኢትዮጵያ እውነት ለመላው ዓለም ለማሳወቅ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ እውነት ለመላው ዓለም ለማሳወቅ እየተሰራ ነው
ባህር ዳር ፤ ጥቅምት 19/ 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ እውነት ለመላው ዓለም በማሳወቅ ምዕራባዊያን በሀገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት የሚያደርጉትን ጫና ለመቋቋም እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ዲያስፖራ የተግባር ምክር ቤት አስታወቀ።
ዲያስፖራው ኢትዮጵያ የገጠማትን ወቅታዊ ችግር ለመፍታት ከመረባረብ በተጨማሪ የዓባይ ግድብን ለማጠናቀቅ ገንዘብ በማዋጣት አላማውን ተግባሩን በተግባር እያሳየ እንደሚገኝም ተመልክቷል።
ነዋሪነታቸው በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ሎሳንጀለስ ከተማ ያደረጉት የኢትዮጵያ ዲያስፖራ የተግባር ምክር ቤት ሊቀመንበር አቶ ዓለምአየሁ አበበ፤ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት እየተስተዋለ ያለው ጫና ተገቢ ያልሆነና በማንም አካል መወገዝ ያለበት ነው ብለዋል ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት።
በአሜሪካ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጭምር የመረጧቸው የዴሞክራሲ ፓርቲ ኮንግረስ እና ሴናተሮች በሀገሪቱ ተጽዕኖ ለማድረግ እየጣሩ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህነኑ ከእውነት የራቀ ጫና ለመከላከል የዲያስፖራ ተግባር ምክር ቤቱ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ነው ያመለከቱት።
ከሁለት ወራት በኋላ እዚያው በሚካሄደው ምርጫም 800 ሺህ የሚሆኑና የመምረጥ እድሉ ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተጽዕኖ ለማሳደር ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
አሁን ላይ የህወሓት አሸባሪ ቡድን "ሎቢስቶችን" በመጠቀም በተሰሳተ መረጃ ዓለምን በማደናገር በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲፈጠር እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህንን ችግር ለመቀልበስም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
እየደረሰ ያለው ተገቢ ያልሆነ ጫና ውጭ ባሉ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ላይ ትልቅ ቁጭት ፈጥሯል ያሉት አቶ ዓለምአየሁ፤ ቁጭታቸውንም በተግባር በማሳየት ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
አሁን ላይ የኢትዮጵያ መንግስት ያሉበትን ጫናዎች በመረዳትም ዲያስፖራው ገንዘብ በማዋጣት "ሎቢስት" ቀጥሮ ተጽኖውን ለመቀልበስ በመስራት ላይ እንደሚገኝ አመላክተዋል።
በዚህም የኢትዮጵያ ዲያስፖራ የተግባር ምክር ቤት ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን የአሜሪካ የህግ አስፈጻሚ አካላትን(ኮንግረስና ሴናተሮችን) የተሳሳተ አስተሳሰብ ለመለወጥም እንዲሁ።
በተለያዩ የውጭ ሃገራት ሦስት ሚሊዮን ዲያስፖራ እንደሚኖር የገለጹት አቶ ዓለምአየሁ፤ በመተባበር የታሰበውን ሁሉ ማሳካት ይቻላል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በውጭ ዲፕሎማሲው እየደረሰባት ያለውን ከፍተኛ ጫና ለመቀልበስ ዲጅታል ዲፕሎማሲ ተመስርቶ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በእንግሊዝ የሚኖሩት የምክር ቤቱ ስራ አስፈፃሚ አባል አቶ አለባቸው ደሣለኝ ናቸው።
ዛሬ ኢትዮጵያ በምዕራቡ አለም እየደረሰባት ላለው ያልተገባ ጫና በዲፕሎማሲው ዘርፍ ክፍተቶች በመኖራቸው እንደሆነ ጠቅሰው፤ ለዚህም አኩራፊ በነበሩ ዲፕሎማቶች ተወክላ በመቆየቷ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ወክላቸው የነበሩ ዲፕሎማቶች ለኢትዮጵያ ጥብቅና መቆም ሲገባቸው ለግል ፍላጎታቸው ብቻ ሲሰሩ በመቆየታቸው ሀገሪቱ በውጭ ጫና ያልተገባ ተጽዕኖ ውስጥ እንድትገባ ማድረጉን አስረድተዋል።
አሁን ላይ መንግስት ማስተካከያዎችን እያደረገ በመሆኑ ችግሩ እንደሚቃለል እምነቱ እንዳላቸው የገለጹት አቶ አለባቸው፤ በመላው አለም የሚገኘው ዲያስፖራም ጫናውን ለመቀልበስ በቁጭት እየታገለ ነው ብለዋል።
ዲያስፖራው አስፈላጊ ከሆነም እዚህ መጥቶ እስከ ግንባር ድረስ በመሰለፍ አሸባሪውን ለመፋለም መነሳሳቱንና ይህም በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ እንደማይደራደር የሚያሳይ መሆኑን አመልክተው፤ ይህን አስቸጋሪ ወቅት በማለፍም ድሉ የኢትዮጵያዊያን እንደሚሆን አንጠራጠርም ሲሉ ገልጸዋል።
በአሜሪካን ሀገር የሚኖረው ዲያስፖራ ስለኢትዮጵያ እውነት በየጊዜው ድምጹን በሰልፍና በጽሁፍ ለሚመለከተው አካል በማሰማት ላይ እንደሚገኝ ያመለከቱት ደግሞ ነዋሪነታቸውን በዋሽንግተን ዲሲ ከተማ ያደረጉት የምክር ቤቱ አባል ወይዘሮ አምሣለ ገሰሰ ናቸው።
ዋሽንግተን ዲሲ የአሜሪካ ዋና ከተማ እንደ መሆኗ ዲያስፖራው ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ላይ የተሳሳተ ግንዛቤ ለያዘው የአሜሪካ መንግስት በየጊዜው ድምጹን በማሰማት ላይ ይገኛል ነው ያሉት።
ይህ ደግሞ ትልቅ ለውጥ እያመጣ መሆኑን የተናገሩት ወይዘሮ አምሣለ ኢትዮጵያን ካልተገባ ጫና እንድትወጣ የማድረግ ሁሉን አቀፍ ትግል ተጠናክሮ እንደሚቀጠል አስታውቀዋል።
አሸባሪው የህወሓት ቡድን በሀገር ላይ የከፈተው የእብሪት ጦርነት ኢትዮጵያዊያንን አንድ በማድረግ ሁሉም ለሀገሩ ሉዓላዊነት እንዲቆም ማስቻሉን አመልክተዋል።
"ኢትዮጵያ የገጠማትን ሁሉ ፈተና በልጆቿ የተባበረ ክንድ በድል እንደምትሻገር ተስፋ አለኝ " ብለዋል።
ዲያስፖራው ማህበረሰብ ኢትዮጵያ የገጠማትን ወቅታዊ ችግር ለመፍታት ከመረባረብ በተጨማሪ የዓባይ ግድብን ለማጠናቀቅ ገንዘብ በማዋጣት የተለመደ ተሳትፎውን በተግባር እያሳየ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
የምክር ቤቱ አመራሮች ለመከላከያ ሰራዊቱ ድጋፍ ለማድረግና የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጥበበ-ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን ለመጎብኘት በባህር ዳር ከተማ እንደሚገኙ ተዘግቧል።