በዓለም የወጣቶች የቦክስ ውድድር ኢትዮጵያን የሚወክሉት ቦክሰኞች ወደ ሀንጋሪ ያቀናሉ - ኢዜአ አማርኛ
በዓለም የወጣቶች የቦክስ ውድድር ኢትዮጵያን የሚወክሉት ቦክሰኞች ወደ ሀንጋሪ ያቀናሉ
አዲስ አበባ ነሃሴ 12/2010 በሀንጋሪ ርዕሰ መዲና ቡዳቤስት በሚካሄደው 6ኛው የዓለም ወጣቶች የቦክስ ውድድር ኢትዮጵያን ወክለው የሚወዳደሩት እንዳሻው አላዩና ሀና ደረጀ ዛሬ ሌሊት ወደ ስፍራው ያቀናሉ። የቦክስ ውድድሩ ከነሐሴ 15 እስከ 25 ቀን 2010 ዓ.ም ይካሄዳል። የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን የውድድርና ስልጠና ከፍተኛ ባለሙያ ስንታየሁ ተስፋዬ ለኢዜአ እንደገለጹት በሀንጋሪው ውድድር ኢትዮጵያን ወክለው የሚሳተፉት ቦክሰኞች ዛሬ ከሌሊቱ 5 ሰዓት ወደ ውድድሩ ስፍራ ያቀናሉ። እንዳሻው አላዩ በ49 ኪሎ ግራም እንዲሁም ሀና ደረጀ በ48 ኪሎ ግራም ኢትዮጵያን ወክለው እንደሚሳተፉም ተናግረዋል። ሁለቱ ቦክሰኞች በሀንጋሪው ውድድር መሳተፍ የቻሉት ከሚያዝያ 27 እስከ ግንቦት 5 ቀን 2010 ዓ.ም በሞሮኮ ካዛብላንካ ከተማ በተካሄዳው የአፍሪካ የወጣቶች የቦክስ ውድድር የወርቅ ሜዳሊያ በማግኘታቸው እንደሆነ ጠቅሰዋል። ቦክሰኞቹ ለውድድሩ ቅድመ ዘግጅት ይረዳቸው ዘንድ ከነሐሴ መጀመሪያ ጀምሮ በአሰልጣኝ ከድር ከማል አማካኝነት ልምምድ ሲያደርጉ መቆየታቸውንም ነው አቶ ስንታየሁ ያስረዱት። እንዳሻው አላዩና ሀና ደረጀ በአህጉራዊ ውድድር አሸናፊ ከሆኑ በኋላ በውድድሩ የሚሳተፉ መሆናቸውንና በዚህ ረገድም ቦክሰኞቹ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን አፍሪካን ወክለው እንደሚወዳደሩም አስረድተዋል። ቦክስ ኢትዮጵያ በአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መድረኮች ላይ ከምትሳተፍባቸው ስፖርቶች አንዱ ሲሆን የሜዳሊያ ባለቤትም እየሆነች ነው። ከአራት ወር በፊት በሞሮኮ ካዛብላንካ በተካሄደው የአፍሪካ ወጣቶች የቦክስ ሻምፒዮና ውድድር ኢትዮጵያ የሦስት ሜዳሊያዎች ባለቤት በመሆን አመርቂ ውጤት አስመዝግባለች። በዘርፉ እውቀት ያላቸው ስፖርተኞችን ለማፍራት የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ለተወዳዳሪዎች በአገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መድረኮች እንዲሳተፉ እድል እየፈጠረላቸው ይገኛል።