መምህራን ለሀገር ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
መምህራን ለሀገር ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ተጠየቀ
አርባ ምንጭ፤ ጥቅምት 19/2014 (ኢዜአ) መምህራን ለሀገር ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ጥሪ አቀረበ፡፡
ዓለም አቀፍ የመምህራን ቀን በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እየተከበረ ነው፡፡
የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሐንስ በንቲ ለኢዜአ እንደገለጹት ለሰላም መረጋገጥ ትምህርት ትልቁ መሣሪያ ነው።
ሰላም ሲደፈርስ በትውልድ አዕምሮ ላይ ጥሎት የሚያልፈው ጠባሳ ከፍተኛ በመሆኑ በሁሉም እርከን ትምህርት ቤቶች የሚገኙ መምህራን ስለሰላም እንዲያስተምሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በህወሓት የሽብር ቡድን ወረራ ምክንያት ከ7 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች መውደማቸውን የጠቆሙት ዶክተር ዮሐንስ፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ከትምህርት ገበታቸው መፈናቀላቸውን አስታውቀዋል።
ጦርነት በሌለባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ትምህርት ቤቶችም የተፈናቃይ ዜጎች መቆያ በመሆናቸው የትምህርቱን ዘርፍ በእጅጉ መጉዳቱን አመልክተዋል።
የሙያ ማህበሩ የተፈናቀሉ ተማሪዎችንና መምህራንን መልሶ ለማቋቋምና ተፈናቃይ ተማሪዎች ባሉበት ሆነው ትምህርት እንዲያገኙ የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን ጠቁመው፤ ለዚሁ ተግባር ሁሉም አካል የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ መምህርትና በሰላም ዙሪያ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት ዶክተር ድሪቧ ደበበ በበኩላቸው ትምህርት ያለሰላም ሊሳካ እንደማይቻል አመልክተዋል።
ትምህርት የትውልድን ዕውቀት፣ አመለካከትና ክህሎትን በማዳበር ለሰላም ቁልፍ መሣሪያ መሆኑን ተናግረዋል።
"ትምህርት የሰው ልጅን ክፉ አድርጎ አይቀርጽም" ያሉት ዶክተር ድሪቧ፤ ''በአገራችን ሰላማችን እየተመሰቃቀለ ያለው እኛ መምህራን የሚጠበቅብንን ሃላፊነት በአግባቡ ባለመወጣታችን ምክንያት ነው'' ብለዋል፡፡
የቀድሞ የትምህርት ስርዓት የአገርን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ ሳይሆን በውጭ ተሞክሮ ላይ የተንጠለጠለ በመሆኑ ለሰላም መስፈን የሚያግዝ እንዳልነበር አስታውሰዋል።
የማህበረሰቡ እውቀት፣ ልማድና አስተሳሰብ እንዲሁም የሃይማኖት ተቋማትና የባህል መሪዎች ሰላምን በማስፈን ረገድ የድርሻቸውን እንዲወጡ የሚያደርግ ምቹ ሁኔታ አለመኖሩን ጠቅሰዋል።
ዛሬ በአገሪቱ አንድ ጫፍ የተፈጠረው የሰላም እጦት ወደሌላ አካባቢ የማይስፋፋበት ምንም ዋስትና የለም'' ያሉት ዶክተር ድሪቧ፤ መምህራን ለአገር ሰላም በጥልቀት በማሰብ የማስተማርና የመከላከል ስራ መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።
ህዝብና አገር ተለያይቶ የሚታይ አለመሆኑንና አገር በቀላሉ የሚፈርስ አለመሆኑን ትውልዱ እንዲረዳ በማድረግ እንዲሁም ለሀገር ዘላቂ ሰላም አዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ጉልህ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን ያስረዱት ደግሞ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አበበ ናቸው፡፡
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሙያ ማህበሩ ፕሬዝዳንት ዶክተር ነብዩ የማነ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ስራውን ሰላማዊ በማድረግ ግንባር ቀደም መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ለአገር ዘላቂ ሰላምና ለመማር ማስተማር ሥራው ውጤታማነት የመምህራን ድርሻ የጎላ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ነብዩ፤ ተማሪዎችም ለሰላም ዘብ ሊቆሙ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ28ኛ ጊዜ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ለ25ኛ ጊዜ በተከበረው ዓለም አቀፍ የመምህራን ቀን ከወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር ተያያዥነት ያላቸው 16 ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በስነ ስርአቱ ላይ ከሁሉም ክልሎችና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተወከሉ የሙያ ማህበሩ ስራ አስፈጻሚ አካላት ተሳትፈዋል።