ለህልውና ዘመቻው ስኬታማነት የሚዲያዎች ሚና መጠናከር አለበት - ኢዜአ አማርኛ
ለህልውና ዘመቻው ስኬታማነት የሚዲያዎች ሚና መጠናከር አለበት
ጥቅምት 19 ቀን 2014 (ኢዜአ) ለህልውና ዘመቻው የህዝቡ ድጋፍ እንዲጠናከርና የኢትዮጵያ እውነታ ለዓለም ተደራሽ እንዲሆን የሚዲያዎች ሚና መጠናከር እንዳለበት ተገለጸ፡፡
የኢሳት ቴሌቪዥን ማኔጂንግ ዳይሬክተር እና የናሁ ቴሌቪዢን ስራአስኪያጅ ወቅታዊ ጉዳዮችን በማስመልከት ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
የኢሳት ቴሌቪዢን ማኔጂንግ ዳይሬክተር ደረጄ ተክሌ ሚዲያዎች እውነትን ለማህበረሰቡ ማስረጽ የመጀመሪያ ተግባራቸው መሆን እንዳለበት አስገንዝቧል።
ለህልውና ዘመቻው የህዝቡ ድጋፍ እንዲጠናከርና የኢትዮጵያ እውነት ለዓለም ተደራሽ እንዲሆን የሚዲያዎች ሚና መጠናከር እንዳለበትም ገልጿል፡፡
"ኢትዮጵያ እንደምታሽንፍ ጥርጥር የለውም" በማለት ገልጾ፤ “ህብረተሰቡ በያለበት ለዘመቻው የሚችለውን ሁሉ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል” ብሏል።
የናሁ ቴሌቪዢን ስራ አስኪያጅ ሃና ደምሴ “ሚዲያዎች የህልውና ዘመቻውን እንዲያግዙ ተጨባጭ እና ትክክለኛ መረጃ በፍጥነት ከመንግስት አካል ማግኘት ይኖርባቸዋል” ብላለች።
ሃላፊነት ወስደው የሚሰሩ ሚዲያዎች ትክክለኛ መረጃዎችን በወቅቱ ለህዝቡ ተደራሽ ማድረግ ከቻሉ ህዝቡ በማህበራዊ ሚዲያዎች ለሚነዙ የሃሰት ፕሮፓጋንዳዎች ቦታ አይሰጥም የሚል እምነት እንዳላት ገልፃለች።
ለዚህም ሚዲያዎች ትክክለኛ መረጃ ከትክክለኛ ምንጭ በማምጣት በፍጥነት ተደራሽ ማድረግ እንዳለባቸው ተናግራለች።
ኢትዮጵያ የጀመረችውን የህልውና ዘመቻ በአሸናፊነት የምታጠናቅቅበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን ጠቅሳ፤ “ከዘመቻው መጠናቀቅ በኋላም ሚዲያዎች ብዙ ስራ ይጠብቃቸዋል” ብላለች።