ሽፍቶች ተደምስሰው ወደቄያችን ብንመለስ ከተረጂነት እንወጣለን--- የመተከል ተፈናቃዮች - ኢዜአ አማርኛ
ሽፍቶች ተደምስሰው ወደቄያችን ብንመለስ ከተረጂነት እንወጣለን--- የመተከል ተፈናቃዮች
አሶሳ ፣ ጥቅምት 19/2014 (ኢዜአ) ሽፍቶች ተደምስሰው ወደቄያችን ብንመለስ ከተረጂነት እንወጣለን ሲሉ የመተከል ተፈናቃዮች ተናገሩ።
በሽብር ተግባር የተሰማራው የህወሓት የጥፋት ቡድን ኢትዮጵያን የማፈራረስ ህልሙን ለማሳካት ትኩረት ካደረገባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች አንዱ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ነው፡፡
በክልሉ የሚገኘው መተከል ዞን ደግሞ የቡድኑ ዋነኛ የጥፋት ዕቅዱ ኢላማ እንደሆነ የክልሉ ህዝብ እና መንግስት በተደጋጋሚ ሲገልጹ ይደመጣል።
በነሐሴ ወር 2011 ዓ.ም በዳንጉር ወረዳ አይሲካ ቀበሌ በሁለት ግለሰቦች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት በመተከል ዞን ተከስቶ የነበረው ግጭት በአሸባሪው ህወሓት ተላላኪዎች የብሔር መልክ እንዲይዝና ወደ ካማሽ እና ሌሎችም የክልሉ አካባቢዎች እንዲዛመት ለማድረግ ጥረት ተደርጓል፡፡
በዚህም በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ካደረሰው ቀውስ ባለፈ ግጭቱ ረዘም ላለ ጊዜ እንዲቀጥል ማድረጉ የሚታወስ ነው።
ተከስቶ በነበረው ግጭት በሰዎች ሕይወት እና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፡፡
በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የዞኑ ነዋሪዎች ከቄያቸው በመፈናቀል ለችግር መዳረጋቸውም እንዲሁ።
የፌደራል መንግስት የመተከል ዞን ሰላም ለመመለስ ኮማንድ ፖስት ከማቋቋም ጀምሮ ከክልሉ መንግስት ጋር በመቀናጀት ባደረገው ጥረት በአሁኑ ወቅት በዞኑ አንጻራዊ ሠላም እየሰፈነ መጥቷል ማለት ይቻላል፡፡
በአካባቢው እየሰፈነ ላለው ሰላም የሃገር መከላከያ ሠራዊት፣ የፌደራል ፖሊስና የክልሉ ልዩ ሃይሎች የከፈሉት መስዋዕትነት ከፍተኛ ድርሻ አለው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህም የጋምቤላ፣ የአማራ፣ የደቡብ፣ የሲዳማ እና ሌሎች ክልሎች ልዩ ሃይሎቻቸውን ወደ አካባቢው ከመላክ ጀምሮ ችግሩን ለማስቆም እስከ ህይወት መስዋዕትነት ድረስ በመክፈል እያደረጉት ያለው ድጋፍ የሚጠቀስ ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን እንደ አይናቸው ብሌን የሚያዩት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መገኛ በሆነው መተከል ዞን የተከሰተው ግጭትና አለመረጋጋት እየቀነሰ መጥቶ የአካባቢው ሠላም ቢሻሻልም ግጭቱን በዘላቂነት የማስቆሙ ሥራው ሌላ ተጨማሪ ጥረትን ይጠይቃል፡፡
በግጭቱ የተፈናቀሉ ዜጎችን በዘላቂነት መልሶ የማቋቋም ጉዳይም እንዲሁ የሁሉንም ትኩረት የሚሻ ነው።
ተከስቶ በነበረው ግጭት በዞኑ ከተፈናቀሉት ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ከድጃ ደሳለኝ አንዷ ናቸው።
እንደ ዛሬው ለችግር ከመዳረጋቸው በፊት በግብርና ስራ ልጆቻቸውን በሚገባ ከመመገብ ባለፈ ኑሯቸውንም በተሻለ ሁኔታ ይመሩ እንደነበር በቁጭት ያስታውሳሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት በአሶሳ ዞን ባምባሲ ወረዳ በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ እየኖሩ ያሉት ተፈናቃዩዋ “አሁን ሁለት ልጆቼን በሚገባ መመገብ አለመቻሌ ብቻ ሳይሆን ሲታመሙ ማሳከምም አልቻልኩም” በማለት በግጭቱ ምን ያህል ለከፋ ችግር መዳረጋቸውን ይናገራሉ፡፡
ወደ ቄያቸው የመመለስ ህልም ቢኖራቸውም ከመመኘት ባለፈ እውን ይሆናል የሚል እምነት እንደሌላቸው ነው የገለጹት።
አካባቢያቸው ሙሉ ለሙሉ ወደ ቀደመ ሰላሙ አለመመለሱ ደግሞ ለእዚህ እንደ አንድ ምክንያት ይጠቅሳሉ።
ወደ ቀያቸው ተመልሰው አሊያም አሁን በሚኖሩበት አካባቢ ተደራጅተው ራሳቸውን እንዲችሉ ቢደረግ የተሻለ መሆኑንና ከተረጂነት ህይወት ለመውጣት እንደሚያስችላቸው ነው ያመለከቱት።
"በምኖርበት አካባቢ ተከስቶ በነበረ ግጭት ቅያሪ ልብስ እንኳን ሳልይዝ በምሽት ወጥቼ ጫካ ገብቼ ነው ሕይወቴን ያዳንኩት" ያሉት ደግሞ ሌላው ተፈናቃይ አቶ ሃሰን ሽመልስ ናቸው፡፡
የግጭቱ ምክንያት የግል ጥቅም ያሰከራቸው የሽብርተኛው ህወሓት የጥፋት ቡድን አስፋጻሚ ሽፍቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ተፈናቃዩ እንዳሉት በጥፋት ቡድኑ እኩይ ድርጊት ህጻናት፣ አቅመ ደካሞች እና ነፍሰጡር እናቶች ጭምር ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ሲገደሉ በርካታ ንብረትም ተዘርፏል፤ ወድሟልም፡፡
አሁን በሚኖሩበት የባምባሲ ጊዜያዊ መጠለያ ህይወታቸውን እያቆዩ ያሉት የአካባቢው ህብረተሰብ ያለውን እያካፈላቸው ነው።
በዚህም የመኖር ተስፋቸው በማደጉ የተጀመረው ድጋፍ በቀጣይ በዘላቂነት እስኪቋቋሙ ድረስ እንዲቀጥል ይፈልጋሉ። ሁሉም ኢትዮጵያዊ ድጋፉን እንዲያጠናክርም ተማጽነዋል።
“ሽፍቶች በማያዳግም ሁኔታ ተደምስሰው ወደቄያችን ብንመለስ ለመንግስት እና ለማህበረሰቡ ሸከም ሆኖ ከመኖርና ከተረጂነት ህይወት እንላቀቃለን” ሲሉ እምነታቸውን ገልጸዋል።
በአካባቢያቸው ተከስቶ በነበረው ግጭት ምክንያት ከረጂነት ወደ ተረጂነት ህይወት መግባቱን የተናገረው ደግሞ ወጣት መሃመድ ኢማም ነው፡፡
“በመጠለያ ጣቢያው ምግብ እና ሌሎች ድጋፎችን በየወሩ እያገኘሁ ነው፤ ሰርቼ ራሴን መቀየር እየቻልኩ የሌሎች ተመጽዋች በመሆኔ ደስተኛ አይደለሁም፤ ጭንቀትም ሆኖብኛል” ብሏል።
አሁን ባለበት አካባቢ ከወጣቶች ጋር በመደራጀት ሰርቶ የመቀየር ህልሙ እንዲሳካ መንግስት ለወጣቶች ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቋል።
"በክልሉ በተለይ የመተከል ዞን ግጭት ሦስት ዓመታትን አስቆጥሯል" ያሉት ደግሞ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ታረቀኝ ታሲሳ ናቸው።
እሳቸው እንዳሉት በግጭቱ ከ493 ሺህ በላይ ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። ከተፈናቀሉት መካከል ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑት የመተከል ዞን ነዋሪዎች ናቸው፡፡
ሌሎቹ ተፈናቃዮች ከካማሽ ዞን ወረዳዎች እንዲሁም ከአሶሳ ዞን ኦዳቡልድግሉ ወረዳ እና ከአጎራባች የኦሮሚያ ክልል ባቦ፣ ቡሊሶ እና ቆንዳላ ወረዳዎች ተፈናቅለው ወደ ክልሉ የገቡ ሲሆኑ በአሁኑ ወቅት ሁሉም ተፈናቃዮች ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ እርዳታ ጠባቂ ሆነዋል፡፡
ኮሚሽነሩ ተፈናቃዮችን ከአጎራባች ክልሎች በመመለስ በጊዜያዊ መጠለያ ለማሰባሰብ ባደረገው ጥረት ውጤት መገኘቱን ነው የተናገሩት፡፡
"ለተፈናቃዮች ዕለታዊ ድጋፍ በማቅረብ የሞት አደጋ እንዳይከሰት እየተሰራ ነው፤ ይሁን እንጂ የድጋፍ አቅርቦት ስራውን ለማጠናከርና ችግሩ በሚገባ እንዲታወቅ የተከናወነው የቅስቀሳ ሥራ በሚፈለገው ልክ አይደለም" ብለዋል።
እንደ ኮሚሽነር ታረቀኝ ገለጻ የክልሉን ተፈናቃዮች በዘላቂነት ለማቋቋም በቀጣይ አምስት ዓመት የሚተገበር ስትራቴጂክ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ ተገብቷል።
"ስትራቴጂክ ዕቅዱ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው በመመለስና ቋሚ መኖሪያ ቤት እንዲገነባላቸው ማድረግን አካቶ የያዘ ነው፤ የውሃ፣ የጤና፣ የመንገድ እና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን የማስፋፋት ስራዎችን ማከናወንም እንዲሁ በስትራቴጂክ ዕቅዱ የተካተቱ ናቸው" ሲሉ አመልክተዋል።
በእቅዱ የወደሙ መሰረተ ልማቶች መልሰው የሚገነቡ ሲሆን ከጸጥታ ሃይሎች ጋር በመቀናጀትም የተዘረፉ የተፈናቃዮች ንብረቶችን የማስመለስ ስራ እንደሚሰራ ኮሚሽነር ታረቀኝ አመልክተዋል፡፡
ኮሚሽነሩ እንዳሉት ለተጎጂዎች ድጋፍ ለማድረግ እየተከናወነ ባለው ስራ የመንግስትን ክፍተት በመሙላት በኩል መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ያደረጉት አስተዋጽኦ የሚበረታታ ነው። ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም በጠቅላላው ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
ይህንን ድጋፍ ለማጠናከር በክልሉ የሚገኙ በጎ አድራጊ ድርጅቶች የሚያከናውኗቸው ፕሮጀክቶች ተፈናቃዮችን በዘላቂነት መልሶ ማቋቋም ላይ እንዲያተኩሩ ለማድረግ በስትራቴጂክ ዕቅዱ ተካቶ ይሰራል፡፡ለተረጂዎች የሚደርሱ ድጋፎችን ፍትሃዊ ማድረግም በዕቅዱ ትኩረት የተሰጠው ነው።
ሠላም ሚኒስቴር፣ ብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን፣ የመተከል ኮማንድ ፖስት የስትራቴጂክ እቅዱ አፈጻጸም ዋነኛ አጋሮች እንደሆኑም ነው ኮሚሽነሩ የገለጹት።
እንደ እሳቸው ገለጻ በአሁኑ ወቅት የጸጥታ ሃይሎች በተለይ በመተከል እና ካማሽ ዞኖች ለህግ ማስከበር ሥራ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ ነው፡፡ በእዚህም የመተከል ሠላም ከጊዜ ወደ ጊዜ ተስፋ ሰጪ ሁኔታ እየታየበት መጥቷል፡፡
ኮሚሽነር ታረቀኝ እንዳሉት በክልሉ በግጭቱ ለተፈናቀሉ ወገኖች በአግባቡ ድጋፍ የሚያቀርቡ በጎ አድራጊ ደርጅቶች የመኖራቸውን ያህል መቀመጫቸውን አዲስ አበባ አደርገው “የክልሉ የጸጥታ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ ስላልሆነ ወደ አካባቢው እንድንገባ ዋስትና ይሰጠን” የሚሉ ድርጅቶች አሉ።
"የድጋፍ ስራዎችን ለሚያስተጓጉሉ እነዚህና መሰል ችግሮች ተግባራዊ መፍትሔ በመስጠት ስትራቴጂክ እቅዱን በአግባቡ ስራ ላይ ለማዋል የክልሉ መንግስት አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ በትኩረት እየሰራ ነው" ሲሉ ኮሚሽነሩ አስረድተዋል፡፡
የክልሉ የጸጥታ ምክር ቤት ሰሞኑን በአሶሳ ከተማ የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የፌደራል ፖሊስ እና የክልሉን የጸጥታ አስከባሪ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮችን በማሳተፍ ውይይት አካሂዷል፡፡
በመድረኩ ባለፉት ሦስት ወራት በተከናወኑ ስራዎች በክልሉ በተለይም በመተከል ዞን የሰዎችን ጅምላ ጭፍጨፋና መፈናቀል ማስቆም እንደተቻለ ተገልጿል።
የጸጥታ አስከባሪ ሃይሎችን ለማጠናከር እና ህብረተሰቡ ተደራጅቶ ራሱን እንዲጠብቅ የተደረገው ጥረት በተለይም መተከልን ከዓመታት የጸጥታ ችግር አላቆ ወደ አንጻራዊ ሠላም መመለሱን ነው ምክር ቤቱ ያስረዳው፡፡
በተለይም በዞኖቹ የህግ የበላይነትን በማስጠበቅ የዞኑን የቀደመ ሠላም ሙሉ ለሙሉ በመመለስ የሰዎችን ሞት ማስቀረት ላይ ያተኮረ እቅድ በምክር ቤቱ መዘጋጀቱ ተመላክቷል።
በዕቅዱ ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ማቋቋም አጽንኦት የተሰጠው ጉዳይ ሲሆን በተለይ የክልሉን አዋሳኝ አካባቢዎች ከጠላት እንቅስቃሴ ነጻ ማድረግ ሌላው በምክር ቤቱ በትኩረት የሚሰራበት ጉዳይ ነው።
በተጨማሪም እርቀ ሠላምን በማጠናከር በተደራጀ የህዝብ ግንኙነት ስራ የዞኖቹን ነዋሪዎች አብሮነት ማጠናከር በምክር ቤቱ የሚከናወን ተግባር ነው። እቅዱ በሚቀጥሉት ሦስተ ወራት ተግባራዊ እንደሚደረግ ተመላክቷል፡፡
ለአፈጻጸሙ በየደረጃው የሚገኙ የጸጥታ አስከባሪ አካላት ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ህብረተሰቡን ያሳተፈ ቅንጅታዊ አሰራር እንደሚከተሉ ተመላክቷል።