ዩኒቨርሲቲዎች ሰላማዊ የመማር ማስተማር ከባቢ ሁኔታ ለመፍጠር ከወትሮ የተለዩ ሥራዎች እያከናወኑ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲዎች ሰላማዊ የመማር ማስተማር ከባቢ ሁኔታ ለመፍጠር ከወትሮ የተለዩ ሥራዎች እያከናወኑ ናቸው
ጥቅምት 19/2014 (ኢዜአ) ዩኒቨርሲቲዎች ሰላማዊ የመማር ማስተማር ከባቢ ሁኔታ ለመፍጠር ከወትሮ የተለዩ ሥራዎች እያከናወኑ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ አመራር አባላት ገለጹ።
የደብረ ብርሃን፣ የወለጋና የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶችና ምክትል ፕሬዚዳንቶች ሰላማዊ የመማር ማስተማር ከባቢን ለመፍጠር በተለየ መልኩ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ለከፋ የጸጥታ ችግር ሲጋለጡ መሰንበታቸው ይታወሳል።
በተቋማቱ የሚፈጠሩት ግርግሮች የተማሪዎችን ሕይወት ቀጥፈዋል፤ ለንብረቶች ውድመትም መንስኤ ሆነዋል።
ወትሮውኑ የግጭት ተጋላጭነታቸው የከፋው ዩኒቨርሲቲዎች በሕልውና ጦርነቱ ምክንያት የሴረኞች መጠቀሚያ እንዳይሆኑ በዚህ ዓመት የተለየ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ነው ዩኒቨርሲቲዎቹ የገለጹት።
የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ንጉስ ታደሰ እንደሚሉት፣ ዘንድሮ የቀውስ ጊዜ አመራርን መተግበር ግድ የሚልበት ወቅት ነው።
ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በተለመደውና በመደበኛ አካሄድ ብቻ ሊያጋጥሙ የሚችሉ የጸጥታ ችግሮችን ማቃለል እንደማይቻል አምኖ እየሰራ መሆኑንም አንስተዋል።
ይህው እሳቤ በሁሉም ዘንድ እንዲደርስ ከአስተዳደር ሰራተኞች፣ መምህራንና ከተማሪዎች ጋር በሚሰሩ ስራዎች ላይ መግባባት የሚደረስና ሁሉም የመፍትሔው ባለቤት እንዲሆን የማድረግ ስራም ይሰራል" ብለዋል።
የወለጋ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር መልካ ሂቃም እንደሚናገሩት፤ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱን የሚያውኩ ችግሮች ማቃለል ላይ ትኩረት ይደረጋል።
እነዚህም አጠቃላይ የመማር ማስተማር ሂደቱን ማስተካከል፣ መሰረተ ልማት ማሟላትና የመምህራን ቅጥር የማካሄድ ስራዎች ይከናወናሉ።
ከዚህ ባለፈም በዩኒቨርሲቲው ደረጃ ሊፈቱ የሚገባቸው ለፀጥታ ጉዳዮች ስጋት የሚሆኑትም ፈጥነው የሚታረሙ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የተማሪዎች አደረጃጀቶች ላይ ትኩረት ተደርጎ ለመስራት ማቀዳቸውን የተናገሩት ደግሞ የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ኡጁሉ ኮክ ናቸው።
ዩኒቨርሲቲው ከዚህ በፊት በአሰራር ደረጃ የተገበረው የዩኒቨርሲቲ ማሕበረሰብ ምክር ቤት የተሻለ ውጤት ማምጣቱን ነው ያስታወሱት።
ከዚህ በኋላም የተማሪዎች አደረጃጀቶችን የማሳተፉ ስራ ትኩረት ተሰጥቶት የአመራር አባላት ተሳትፎ የሚጠናከር እንደሚሆን ነው ያነሱት።