በአማራ ክልል በተመረጡ ትምህርት ቤቶች አዲሱ ስርዓተ ትምህርት በሙከራ ደረጃ ሊጀመር ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል በተመረጡ ትምህርት ቤቶች አዲሱ ስርዓተ ትምህርት በሙከራ ደረጃ ሊጀመር ነው
ባህርዳር ፣ጥቅምት 19/2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል በተመረጡ በ61 የ1ኛና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አዲሱን ስርዓተ ትምህርት በሙከራ ደረጃ ለመተግበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው የስርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ዳይሬክተር አቶ ካሴ አባተ ለኢዜአ እንደገለፁት ቢሮው የሙከራ ትግበራውን በህዳር 2014 ዓም ይጀምራል።
በሙከራ ትግበራው በአሸባሪው የህወሃት ወራሪ ኃይል ባልተያዙ በ44 የ1ኛና በ17 የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደሚጀምር ተናግረዋል።
በትምህርት ቤቶቹ በሚጀመረው አዲስ ስርአተ ትምህርት ከ77ሺህ የሚበልጡ ተማሪዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አመላክተዋል።
በትምህርት ቤቶቹ አዲሱን ስርአተ ትምህርት ለመጀመር አጋዥ የመማሪያና ማስተማሪያ መፃህፍት ዝግጅት ተጠናቆ የህትመት ስራ ለማከናወን በሂደት ላይ መሆኑን አብራርተዋል ።
የመማር ማስተማሩን ስራ ለሚያከናውኑ 1ሺህ 639 መምህራንና የትምህርት ባለሙያዎች ስልጠና እንደሚሰጥ አመላክተዋል።
"በሙከራ ትግበራው ወቅት የሚታዩ ችግሮችን ለይቶ በማስተካከል በቀጣይ አመት በሁሉም ትምህርት ቤቶች አዲሱ ስርዓተ ትምህርት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ይደረጋል" ብለዋል።
ቀደም ሲል የነበረው ስርዓተ ትምህርት መልካም ሰብዕናን መቅረፅ የማያስችል እንደነበር ጠቁመው አዲሱ ስርዓተ ትምህርት የተማሪዎችን መልካም ስብዕናን መገንባት የሚያስችል ሆኖ የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ በክልሉ ተማሪዎች ከዕድሜያቸው ጋር ተያያዥነት ያለው ዕውቀትና ክህሎትን በየክፍል ደረጃቸው እንዲያገኙ በሚያስችል መልኩ ትምህርት ቤቶችን እንደገና የማደራጀት ተግባር ይካሄዳል።
"አዲሱ ስርአተ ትምህርት እንደየ ትምህርት አይነቱ ሀገር በቀል ዕውቀትን ባካተተ መልኩ የተቀረጸና ህፃናት በመልካም ስነ-ምግባር ታንፀው እንዲያድጉ በሚያስችል መልኩ የተዘጋጀ ነው" ያሉት ደግሞ በስርዓተ ትምህርት ዝጅቱ የተሳተፉት የቋንቋና ማህበራዊ ሳይንስ ትምህርት ቡድን መሪው አቶ ሙሉጌታ ምስጋናው ናቸው።
ስርአተ ትምህርቱ የ1ኛ ደረጃ ተማሪዎች ሰብዕናቸው ተገንብቶና ታንፀው እንዲያድጉ የሚያስችል ከመሆኑም በላይ ባህላዊ እሴቶችን በአግባቡ አውቀው እንዲያድጉና እንዲያጎለብቱ በማድረግ ድርሻው ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሰባተኛና ስምንተኛ ክፍል የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና የስራና ክህሎት ትምህርት በተጨማሪነት በስርዓተ ትምህርቱ እንዲካተቱ መደረጉን አመልክተዋል።
ቀደም ሲል የታዩ ችግሮች እንዳይደገሙ በየደረጃው የሚገኙ መምህራን በስርዓተ ትምህርት ዝግጅቱ እንዲሳተፉ መደረጉን ቡድን መሪው አስታውቀዋል።
በአማራ ክልል ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል ከ6 ሚሊዮን የሚበልጡ ተማሪዎች እንደሚገኙ ከቢሮው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።