በጋምቤላ ክልል የልጅነት ልምሻ መከላከያ ክትባት መሰጠት ጀመረ

62

ጋምቤላ ጥቅምት 19/2014 (ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል የልጅነት ልምሻ መከላከያ ክትባት መሰጠት ጀመረ።


የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ታች ኮንግ ዛሬ ክትባቱን ሲያስጀምሩ ለኢዜአ እንዳስታወቁት ክትባቱ ለአራት ተከታታይ ቀናት በክልሉ ሁሉም ወረዳዎች በቤት ለቤትና በሰባት የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች በዘመቻ ይሰጣል።

ክትባቱ እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ከ137 ሺህ በላይ ህፃናት እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ በተለይም ወላጆች ልጆቻቸውን በማስከተብ ለዘመቻው ስኬታማነት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በቢሮው የጤናና ድንገተኛ አደጋዎች ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክትር አቶ ኝኬዎ ጊሎ ክትባቱን ከሚወስዱት ህፃናት መካከል 49 ሺህ 126ቱ በስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ መሆናቸውን አመልክተዋል ።

"ክትባቱን መስጠት ያስፈለገው ባለፈው ዓመት በክልሉ በሚገኝ የስደተኛ መጠለያ ጣቢያ አንድ በበሽታው የተጠቃ ህፃን በመገኘቱና የበሽታውን አስከፊነት ታሳቢ በማድረግ ነው" ብለዋል።

በኢትዮጵያ 17  ነጥብ 9 ሚሊዮን ሕጻናትን ለመከተብ የታቀደበት ዘመቻ በዚህ ወር መጀመሩ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም