ቀጥታ፡

አየር ኃይሉ በተመረጡ ቦታዎች ላይ እያደረገ ያለው ድብደባ የአሸባሪው ሕወሓት አቅምን በማዳከም ረገድ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ አለው

ጥቅምት 19/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር ኃይል በትግራይ ክልል በተመረጡ ቦታዎች ላይ እያደረገ ያለው ድብድባ የአሸባሪው ሕወሓት አቅምን በማዳከም ረገድ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ እንዳለው የአሁንና የቀድሞ መከላከያ ሰራዊት አባላት ገለጹ።

የሕይወት መስዋዕትነት እየከፈለ ላለው የአገር መካለከያ ሰራዊት ተገቢውን ክብርና ድጋፍ መስጠት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል አሸባሪው ህወሃት በሚጠቀምባቸው የጦር መሳሪያ ማከማቻና ወታደራዊ ማሰልጠኛዎች ላይ ድብደባ ማድረጉ ይታወቃል።

አየር ኃይሉ የወሰደው እርምጃ የሚፈልገውን ኢላማ በመምታት ረገድ ውጤታማ እንደነበርም የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት አስታውቋል፡፡

ከኢዜአ ቆይታ ያደረጉ የአሁንና የቀድሞ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በጦርነት ወቅት በአየር ድብደባ የሚወሰዱ እርምጃዎች ግብ የጠላትን አቅም ማዳከምና ምንጩን ማድረቅ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ አየር ኃይል በትግራይ ክልል በተመረጡ ቦታዎች ላይ እያደረገ ያለው ድብደባ የአሸባሪውን ሕወሓት አቅም በማዳከም ረገድ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ እንዳለውም ነው የተናገሩት፡፡

እርምጃው የአሸባሪ ቡድኑን የሎጅስቲክ አቅርቦት በማድረቅ የአሸባሪውን ሕወሓት የስበት ማዕከል አቅም በከፍተኛ ሁኔታ የሚያዳክም መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም የአሸባሪ ቡድኑን የጦርነት አካሄድ የሚያዛቡና የሚረብሹ እንደሆኑም ተናግረዋል።

የ"ጠላትን አቅም በማዳከም ለወገን ኃይል የኦፕሬሽን ስራ ምቹ መደላድል ይፈጥራል" ሲሉም ነው የገለጹት።

ጠላት ለጥፋት የሚጠቀምባቸውን የጦር መሳሪያዎች ማውደም ከወታደራዊ ስልት ባሻገር ሕዝብን ከአደጋ ለመታደግ  ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው አመልክተዋል።

ሕዝብ ላይ ጥፋትና ጉዳት የሚያደርሱ ኢላማዎችን መርጦ መምታት ተገቢና ወቅታዊ ወታደራዊ ስልት እንደሆነም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ብርጋዴር ጀኔራል ካሳዬ ጨመዳ የቀድሞ የአገር መከላከያ ሰራዊት፤

ኮሎኔል ተፈራ እሸቴ የአገር መከላከያ ሰራዊት አባል ናሻለቃ ወንዱ ወልዴ የአገር መከላከያ ሰራዊት አባል የህልውና ዘመቻውን በሚመለከት አንዳንድ ግለሰቦች ከሙያቸው ውጪ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን በሚመለከት የሚሰጡት ትንታኔና መረጃ  ተገቢነትና ተቀባይነት የሌለው መሆኑንም አንስተዋል።

ወታደራዊ እንቅስቃሴ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድና ራሱን በቻለ አካሄድ እንደሚመራ ገልጸው፤ ከዚህ አኳያ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን በሚመለከት ያሉ መረጃዎች ለመንግስትና ለሚመለከተው አካል ብቻ መተው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የሕይወት መስዋዕትነት እየከፈለ ላለው የአገር መካለከያ ሰራዊት ተገቢውን ክብርና ድጋፍ መስጠት እንደሚያስፈልግም ነው የገለጹት።

ኀብረተሰቡ ለመከላከያ ሰራዊቱ ያለውን ደጀንነት በማጠንከር የህልውና ዘመቻው በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ወጣቶች የአገር መከላከያ ሰራዊትን በመቀላቀል ለሰራዊቱ አቅም መጠናከር የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

የአገር መከላከያ ሰራዊት ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን ባገናዘበ መልኩ አቅሙን እንዲያሳድግ ለማስቻል የተጀመሩ የማሻሻያ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉም እንዲሁ።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል የትኛውንም ጠላት መመከት የሚያስችል ቁመና ላይ እንደሚገኝ በተደጋጋሚ ጊዜ ሲገልጽ ቆይቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም