ቀጥታ፡

በአማራ ከ131 ሺህ ለሚበልጡ ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ለመስጠት ዝግጅት ተደርጓል-ቢሮው

ባህርዳር ጥቅምት 18/2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ከ131 ሺህ ለሚበልጡ ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ለመስጠት ዝግጅ መደረጉን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና አሰጣጥ አስመልክቶ  ከባለድርሻ አካላት ጋር በባህር ዳር ከተማ ምክክር አካሄዷል።

የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ማተቤ ታፈረ በውይይት መድረኩ ላይ እንደገለጹት በወቅታዊ የፀጥታ ችግር ምክንያት የ2013 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ መልቀቂያ ፈተና ሳይሰጥ ቆይቷል።

የዘንድሮው ብሔራዊ ፈተና በህልውና ዘመቻ ውስጥ ሆኖ የሚካሄድ በመሆኑ በተለየ ሁኔታ  ፈተናውን ለመስጠት  አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

የውይይት መድረኩ  ባለድርሻ አካላት ፈተናው በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ የሚያስችላቸው ተጨማሪ ዝግጅት እንዲያደርጉ የሚያግዝ መሆኑን አመልክተዋል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ሙላው አበበ በኩላቸው በክልሉ  131 ሺህ 167 ተማሪዎች ፈተናውን እንደሚወስዱ አስታውቀዋል።

ለፈተናው 255 መፈተኛ ጣቢያዎች መዘጋጀታቸውን ጠቁመው ከተፈታኝ ተማሪዎች መካከል 123 ሺህ 159 ተማሪዎች የመደበኛ፣ ቀሪዎቹ ደግሞ የግል ተፈታኞ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ለፈተናው ከ4 ሺህ 800 በላይ ፈታኝ መምህራን፣ የጣቢያ ኃላፊዎች፣ የማዕከል አስተባባሪዎችና  ሱፐር ቫይዘሮች  መለየታቸውን አብራርተዋል።

በአሸባሪው ህወሓት ቡድን በወረራ በተያዙ ሰሜን ወሎና ዋግህምራ፣ እንዲሁም በከፊል ደቡብ ወሎ፣ በደሴ ከተማ አስተዳደርና ሰሜን ጎንደር ዞኖች የሚገኙ 32 ሺህ 940 ተማሪዎች ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተናውን እንደማይወስዱ አስረድተዋል።

ተፈታኞች አካባቢዎቹ ከግጭት ነፃ ሲሆኑ ፈተናው በልዩ ሁኔታ ተዘጋጅቶ እንደሚሰጣቸው አስታውቀዋል።

''ወቅቱ የህልውና ዘመቻ ላይ የምንገኝ በመሆኑ የሚሰጠው ፈተና ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከናወን  የፀጥታ ኃይሉ ከመቸውም ጊዜ በበለጠ ጥንቃቄ ያደርጋል'' ያሉት ደግሞ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩ ናቸው።   

በውይይት መድረኩ ላይ በክልልና በዞን ደረጃ የተቋቋመው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ግብረ ኃይል አባለት  ተሳትፈዋል።

የዘንድሮው የ12 ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ከጥቅምት 29 እስከ ህዳር 2 ቀን 2014 ዓ.ም  እንደሚሰጥ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም