የሽብር ቡድኑ እያደረሰ ያለውን ጥፋት በጋራ መመከት ይገባል---የኦሮሚያ ክልል መጅሊስ - ኢዜአ አማርኛ
የሽብር ቡድኑ እያደረሰ ያለውን ጥፋት በጋራ መመከት ይገባል---የኦሮሚያ ክልል መጅሊስ
ደሴ ኢዜአ ጥቅምት 19/2014 የህወሓት ወራሪ ኃይል ኢትዮጵያን ለማፍረስ በአማራና በአፋር ክልሎች እያደረሰ ያለውን ጥፋት ተጋግዞ በጋራ መመከት እንደሚገባ የኦሮሚያ ክልል መጅሊስ አስታወቀ።
መጅሊሱ በኮምቦልቻ ከተማ ለተጠለሉ ተፈናቃዮች 10 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የምግብ፣ የአልባሳትና የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።
የድጋፉ አስተባባሪ ሸህ መሃመድ ዛኪር እንደገለጹት አሸባሪው የህወሓት ቡድን በደረሰባቸው አካባቢዎች ከሰው ልጅ የማይጠበቅ ዘግናኝ ድርጊት ፈጽሟል።
ወራሪው ቡድን ኢትዮጵያን ለማፍረስ በአማራና በአፋር ክልሎች ሁለንተናዊ ጥፋት መፈጸሙን እንደቀጠለም ተናግረዋል፡፡
"በእዚህ የጥፋት ተግባር በሰውና በንብረት ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት የጋራ በመሆኑ ተጋግዘንና ተደጋግፈን ችግሩን መመከትና ማለፍ ይገባናል'' ብለዋል።
የኦሮሚያ ክልል መጅሊስ የሰበታ፣ ቡራዩ፣ ዱካምና ሱሉልታ ከተሞችን እንዲሁም አል ኢህሳን በጎ አድራጎት ማህበርንና ሌሎች አካላትን በማስተባበር 10 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ማድረጉን ሸህ መሃመድ ተናግረዋል።
በድጋፉ ዱቄት፣ ሩዝ፣ ማኮሮኒ፣ ዘይት፣ የምግብ ማብሰያ ቁሳቁስና የተለያዩ አልባሳት ለተፈናቃዮች መለገሳቸውን ተናግረዋል፡፡
"የገጠመው ሀገራዊ ፈተና በድል እስኪያልፍ ድረስ መጅሊሱ ህብረተሰቡን በማስተባበር የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል" ሲሉም አክለዋል።
የመጅሊሱን ድጋፍ የተረከቡት የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ዘሪቱ ሁሴን በበኩላቸው የጥፋት ቡድኑ በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች ዘግናኝ ድርጊት እየፈጸመ መሆኑን ተናግረዋል።
"በተለይ በሴቶችና ህጻናት ላይ የፈጸመው በደል ታሪክ ይቅር አይለውም" ያሉት ኃላፊዋ የተፈናቀሉ ዜጎችን መደገፍና ከጎናቸው መሆን ከሁሉም እንደሚጠበቅ አመልክተዋል፡፡
እንደ ኃላፊዋ ገለጻ መንግስት የተለያዩ አካላትን በማስተባበር የእለት ደራሽ ምግብና ቁሳቁስ ለማቅረብ እየሰራ ቢሆንም ከተፈናቃዮች ቁጥር መጨመር ጋር ተያዞ ከአቅም በላይ እየሆነ ነው።
"የኦሮሚያ ክልል መጅሊስ ያደረገው ድጋፍ ችግሩን በተወሰነ ደረጃ ለማቃለል ያግዛል፤ ለተደረገው ድጋፍም እናመሰግናለን" ብለዋል።
አስተማማኝ ሰላም ሰፍኖ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቄያቸው እስኪመለሱ ድረስ ኢትዮጵያዊያን የጀመሩትን ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያጠናክሩ ወይዘሮ ዘሪቱ ጠይቀዋል፡፡
ከደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽህት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በጥፋት ቡድን ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በኮምቦልቻና ደሴ አካባቢ የተጠለሉ ተፈናቃዮች ቁጥር ከ700 ሺህ አልፏል።