ለልጅ ኢያሱ መምከሪያ የተደረሰው የፊታውራሪ ተክለሃዋርያት ተውኔት - ኢዜአ አማርኛ
ለልጅ ኢያሱ መምከሪያ የተደረሰው የፊታውራሪ ተክለሃዋርያት ተውኔት
           ዕድገት ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ
/አየለ ያረጋል/
ፊታውራሪ ተክለሐዋርያት ተክለማርያም ዘመናዊ ቀለም ከቀሰሙ ቀደምት ኢትዮጵያዊያን አንዱ ናችው። ትውልዳቸው ሸዋ ሲሆን ዕድገታቸው ደግሞ የዳግማዊ ምኒልክ ቀኝ እጅ በሚሰኙት በታላቁ መስፍን ልዑል ራስ መኮንን እልፍኝ ሐረር ነው። ግና በታዳጊነታቸው በአድዋ ዘመቻ የተሳተፉና የጦርነቱን ትዕይንት በግለ ታሪካቸው ያስቃኙ የታሪክ ባለውለታ ናቸው።
ገና በልጅነታቸው በአብነት ትምህርት ቤት በነበራቸው የቀለም አቀባበል የተደነቁት ራስ መኮንን በወቅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ከነበሩ ሩሲያዊ ጋር ለዘመናዊ ትምህርት ወደ ሞስኮ ላኳቸው። በሩሲያ መድፈኝነት ተምረው ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ ለግብርና ትምህርት ዳግም ወደ አውሮፓ ተሻግረው ዕውቀት ቀስመዋል። በዘመናዊ ኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያውን ሕገ መንግስት አርቃቂነት ጨምሮ በተለያዩ የታሪክ ገጾች ጉልህ አሻራ አንብረዋል።
ፊታውራሪ ተክለሃዋርያት ወደ ኢትዮጵያ በተመለሱበት ጊዜ ዳግማዊ ምኒልክ የአልጋ ቁራኛ ሆነው፤ ልጅ ኢያሱም አልጋወራሽ ተሰይመው በፊታውራሪው አባባል 'በልጅነት አገር እመራለሁ ብሎ የሚቦርቅበት ወቅት ነበር'። 'ኦቶባዮግራፊ' በተሰኘው ግለ ታሪካቸው "ዐፄ ምኒልክ በመጨረሻ ዘመናቸው አንደበታቸው ተዘግቶ፣ ከልፍኛቸው ውስጥ አይወጡም... ልጅ ኢያሱ ግን አልጋወራሽ እየተባሉ ይቦርቃሉ፡፡ … እንደዚህ በአንድ ወገን ያፄ ምኒልክን፣ በሌላው የልጅ ኢያሱን አጉል አኳኋን እያሰብኩ መተከዝ አልቀረልኝም፡፡ ይልቁንም ያለፈውን፣ ያሁኑንም የወደፊቱንም የአገራችንን ሁኔታ እየተመለከትኩ ጠሊቅ ሐዘን ተሰማኝ" ይላሉ።
ቀጥለውም "እንግዲያስ የልጅ ኢያሱን ልቡና መማረክ ያስፈልጋል፤ ታዲያ አዕምሮውን መኮትኮት ይቻላል፡፡ እስቲ ልሞክረው፣ ቢሆን መልካም፣ ያልሆነ እንደሆነ ይቀራል፡፡ ኢትዮጵያ እንደ ዕድሏ ትሆናለች፡፡ …ለልጅ ኢያሱ ቁም ነገር የተሞላበት ጨዋታ ላሰናዳላቸው እያልኩ ተመኘሁ፡፡ …እነ ኤዞፕ፣ እነ ላፎንቴን፣ እነ ኪሪሎፍ የጻፉት የአውሬዎች ተረት (ፋብል) ለምሳሌነት ይረዳኛል፡፡ በዚህ ዓይነት በአማርኛ ተረት ለማሰናዳት አሰብኩ፣ ያውሬዎች ተረት የተባለ ግጥም ጻፍኩ" በማለት በኋላ ተረቱን ወደ ቴአትር እንዳሳደጉት ይናገራሉ።
ልጅ ኢያሱም ለምክር የቀረበላችውን ተረት አድምጠው ከመኳንቶቻቸው ጋር ተሳስቀው እንዳሾፉባቸው ይገልጻሉ። ይህ ልጅ ኢያሱን ለመምከር ተጽፎ ግን አልጋ ወራሹን ቀልብ ያልገዛው 'ያውሬዎች ተረት ወይም የአውሬዎች ኮሜዲ መሳለቂያ' የሚሰኘው ድርሰት ነው። ይህ ድርሰት የኢትዮጵያ ዘመናዊ ቴአትር ፈር ቀዳጅ ይሰኛል። የፊታውራሪ ተክለሀዋርያት ፋቡላ ጷጉሜን 3 ቀን 1913 ዓ.ም በቴራስ ሆቴል በተውኔትነት ለመድረክ በቅቷል።
ድርሰቱ ከልጅ ኢያሱ ውድቀት በኋላ በንግስት ዘውዲቱ ዘመን ታትሟል። በርግጥ ይህ ፋቡላ ወደ ቴአትርነት ተለውጦ የታተመበትን ሰበብ ሲያነሱም በወቅቱ አዲስ አበባ ውስጥ በማዘጋጃ ቤቱ ዳይሬክተር (ከንቲባ) ኅሩይ ወልደስላሴ (ብላቴን ጌታ) አማካኝነት ቴአትር እንዲመለከቱ ተጋብዘው ከተመለከቱ በኋላ እንደሆነ እንዲህ ያበራራሉ። "... ዛሬ ማታ በቴራስ ሆቴል የቴአትር ጨዋታ ለማሳየት ተደራጅተናልና መጥተው እንዲያዩልን የሚል ጥሪ መጣልኝ። … ለማየት ቸኩዬ ሄድኩ። ግን ክፉኛ ተሳቀቅሁ።
አዝማሪዎች፣ ዘፋኞች ተሰብስበው አታሞ፣ መሰንቆ፣ ክራር እየመቱ ሲዘፍኑና ሲጨፍሩ አየሁ፤ የልጅ ኢያሱ አስተዳደር በምን ዓይነት እንደተመራ አይቼ አዝኜ አልነበረም? አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ በምን ዓይነት ወደ ሥልጣኔ እንደሚመራ አየሁና የባሰውን አዘንኩ። … ወዲያው አንድ የቴአትር ጨዋታ ለምሳሌ ያህል ለማሰናዳት ተመኘሁ" ይላሉ።
በዚህ ዘመናዊ የኢትዮጵያ ቴአትር አጀማመር ስሌት የኢትዮጵያ ቴአትር /ተውኔት/ አጀማምር አንድ ምዕተ ዓመት /100 ዓመታት/ አስቆጥሯል። ምንም ስንኳ ፊታውራሪ ተክለሀዋርያት በቴአትር አጀማመር ቢመሰገኑም በኢትዮጵያ ቴአትር ቅርጽ ላይ ግን ዘመናዊ የኢትዮጵያ ተውኔት ኢትዮጵያዊ መልክ እንዳይኖረው አድርገዋል በሚል የመስኩ ሊቃውንት ይከራከራሉ። ይህ ተቃርኖ 'የዳበረ ሂስ ባህል ለኪነ ጥበብ ዕድገት' በሚል መሪ ሃሳብ በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ በተካሄደ የባለድርሻ አካላት መድረክ ላይም በጉልህ ተንጸባርቋል።
በአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ አዘጋጅነት የዘርፉ ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ በተደረገው የውይይት መድረክ ላይ የ100 ዓመታት የኢትዮጵያ ዘመናዊ ቴአትር እድገት በሚል የዳሰሳ ጽሁፍ ቀርቧል። የጥናታዊ ጽሁፉ አቅራቢ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ትምህርት ክፍል መምህሩ ዶክተር ተሻለ አሰፋ የኢትዮጵያን ዘመናዊ ቴአትር ሲሄሱ መጤነት፣ ልሂቃዊነት፣ ተኮፋሽነትና ተቸካይነት በሚል አራት ባህሪያት አላብሰውታል።
ከመጤነት አንጻር የኢትዮጵያን ዘመናዊ ቴአትር አጀማመር ከምዕራባዊያን የተኮረጀ፣ ኢትዮጵያዊ መልክ የሌለው ያደርጉታል። ይህም በበጅሮንድ (በኋላ ፊታውራሪ) ተክለሃዋርያት በ1913 ዓ.ም የቀረበው የአውሬዎች ኮሜዲ የሚሰኘው ቴአትር ከኤዞፕ ተረቶች የተቀዳና በውጭ ተዕጽኖ የተዋጠ እንደሆነ አውስተዋል።
በዚህም ፊታውራሪ ተክለሃዋርያት የወደፊቱን የኢትዮጵያ ቴአትር ዕድገት ኢትዮጵያዊ መልክ እንዳይኖረው ወይም 'መጤነት' ባህሪ እንዲያረብበት አድርጓል ሲሉ ሞግተዋል። ከመነሻው ጀምሮ እስካሁን የኢትዮጵያ ቴአትር ከአዳራሾቹ ቅርጽ፣ መጋረጃዎች፣ አልባሳት፣ መስተንግዶ፣ ቁሳቁሶች እና ተክል... አገርኛ እንዳልሆኑ ይልቁኑም ከአውሮፓ የተኮረጁ ያደርጓቸዋል። ተውኔቶቹ በአርስቶትል ቀመር የታጠሩ፤ ገጸ ባህሪያቱ ከአቀንቃኝና ጸረ-አቀንቃኝ መካከል የተወሰኑ እንጂ እንደ ኢትዮጵያ ባህልና እሴት በሁለት ተጻራሪ ሃይላት መካከል ያለን የሽምግልና ልማድ የዘነጉ፣ ግጭቶች የሚፈቱት በፋብሪካ ሰራሽ ውጤቶች (ለምሳሌ በሽጉጥ) እንጂ በኢትዮጵያ አገርኛ ባህል (ለምሳሌ በቅጠል ማስታረቅን) የረሱ ናቸው ሲሉ ተችተዋል።
ያም ሆኖ በቀዳማዊ አጼ ሃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ከቴአትር ይዘት አንጻር ሃይማኖታዊ፣ ስነ ምግባር፣ ትውፊታዊ /አፈ ታሪካዊ ስራዎች ስለነበሩ ኢትዮጵያዊ መልክ እንደነበራቸው አልሸሸጉም። በደርግ ዘመነ መንግስት የኢትዮጵያ ቴአትር ፖለቲካዊ በተለይም በውጭ ከተኮረጀ የሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለም ላይ ያተኮረ እንዲሁም የትርጉም ስራዎች የበረከቱበት ወቅት እንደነበር አንስተዋል።
በዘመነ ኢህአዴግ ደግሞ ቴአትሮች ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ያጠነጠኑ፣ ለትውፊታዊ /ባህል ትኩረት ያልሰጡ ይልቁኑም ትርጉም ስራዎች ላይ ያተኮሩ እንደሆኑ ገልጸዋል። ለማሳያነት ከ1967 እስከ 2011 ዓ.ም ድረስ በሀገር ፍቅር፣ በብሔራዊ፣ በአዲስ አበባ ባህልና ቴአትር አዳራሽ እና በራስ ቴአትር ለእይታ የቀረቡ ቴአትሮችን ተንትነው አቅርበዋል። በዚህም በሀገር ፍቅር 72 በመቶ፣ በብሔራዊ ቴአትር 54 በመቶ፣ በአዲስ አበባ ባህልና ቴአትር 84 በመቶ፣ እንዲሁም በራስ ቴአትር 74 በመቶ ወጥ ስራዎች እንደሆኑ ተንትነው፤ ለታሪካዊ/ትውፊታዊ ቴአትሮች ግን በሀገር ፍቅር 8 በመቶ፣ በብሄራዊ 11 በመቶ፣ በአዲስ አበባ ባህልና ቴአትር 4 በመቶ እንዲሁም በራስ ቴአትር 2 በመቶ ብቻ ድርሻ ነበረው።
ሁለተኛውን የኢትዮጵያ ቴአትር ባህሪ 'ልሂቃዊነት' ብለውታል። የእስካሁን ቴአትር ቤቶች በአዲስ አበባ ብቻ መታጠራቸውን እና የቴአትር ደራሲዎችም ልሂቃን ለአብነትም በአጼ ሃይለስላሴ የፖለቲካና የሃይማኖት ልሂቃን መሆናቸውን አብራርተዋል። በደርግ ዘመን ፖለቲካዊ ቴአትር፤ በኢህአዴግ ዘመን ደግሞ ልማታዊ ቴአትር ላይ ያተኮረ እንደሆነ ገልጸዋል።
ሶስተኛውን የቴአትር ባህሪ 'ተኮፋሽነት' ሲሉት ቴአትሮች ከመድረክ መውረድ አይፈልጉም፤ ተመልካች ወደ መድረክ እንዲመጣ እንጂ፤ ቴአትሩ ወደ ተመልካች ወርዶ ተደራሽነት እንደሌለውም አብራረተዋል። አራተኛው ባህሪ ደግሞ 'ተቸካይነት' ሲሆን 100 ዓመታት ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ቴአትር በአንድ ቅርጽ የተራመደ፣ በእውናዊነት እና ሞት የታጠረ እንጂ አዳዲስ ስልቶች የሌሉበት ብለውታል። አዳዲስ ቴአትር ቤቶች (ከቀደምት ስርዓተ መንግስት ከተመሰረቱት አራት ቴአትር ቤቶች በስተቀር) እንዳልተገነቡ እንደ ጊዜው ሁኔታውን የሚዋጁ ተውኔቶች እንዳልበቀሉም ተችተዋል።
ጥናት አቅራቢው የኢትዮጵያ ዘመናዊ ቴአትርን የነገ ተስፋና ስጋትም ተንትነዋል። በዚህም በብልጽግና ዘመን ለአገር በቀል ዕውቀት እንደ ርዕዮተ ዓለም መወሰዱ፣ ኪነ ጥበብ ከተለጣፊነት ወጥቶ በሚኒስቴር እና በቢሮ ደረጃ የራሱ ዘርፍ ተሰጥቶች በሚኒስትር ዴኤታ እና ምክትል ቢሮ ሃላፊ እንዲመራ መደረጉ፣ አዳዲስ አምፊ ቴአትሮች መገንባታቸው (ለምሳሌ በእንጦጦ እና የወዳጀነት ፓርክ)፣ ነባር ቴአትር ቤቶች እድሳትና ማስፋፊያ ላይ መሆናቸው እና አወቃቅራቸው በአዲስ መደራጀቱን መልካም ተስፋ ብለውታል።
በአንጻሩ ሕገ መንግስቱን ጨምሮ በባህል ፖሊሲዎች ለኪነ ጥበብ በቂ ትኩረት እንዳልተሰጠው ጠቅሰዋል። ለአብነትም በ10 ዓመቱ አገር አቀፍ የፍኖተ ብልጽግና መሪ የልማት ዕቅድ ቁልፍ ዘርፎች ውስጥ ኪነ ጥበብን ያቀፈው ባሕል እንደሌለበት እንዲሁም በቀድሞ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር የ10 ዓመት መሪ ዕቅድ የኪነ ጥበብ ዘርፍ ልማት አንድም ቦታ እንዳልተጠቀሰ አብራርተዋል። በአጠቃላይ የቴአትር ጥበብ ዳግም ሊቃኝ ይገባል ብለዋል። ትውፊታዊ የኢትዮጵያ ክዋኔዎች ትኩረት ሊቸራቸው ይገባል ሲሉም በጥናታቸውን ጥቁምታ ሰጥተዋል።
በዶክተር ተሻለ ጥናት የኢትዮጵያ የ100 ዓመታት የተውኔት ጉዞ በእንዲህ መልኩ ይቅረብ እንጂ ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል ደጋፊም፤ ነቃፊም አፍርተዋል። የቴአትር እውቀት ዓለም አቀፋዊ /ዩኒቨርሳል/ በመሆኑ በፊታውራሪ ተክለሃዋርያት ተውኔት አጀማመር ላይም ምስጋና እንጂ ወቀሳ ሊቀርብባቸው አይገባም የሚሉ አልጠፉም።
ቀሪዎቹ ደግሞ የኢትዮጵያን ነባር አጨፋፈር ተችተው ከኤዞፕ ተረቶች ቅርጽ ተውኔት አቅርበው ለኢትዮጵያ ዘመናዊ ቴአትር በአውሮፓ ቅኝት እንዲራመድ መሰረት ለጣሉት ተክለሃዋርያት (ፊታውራሪ) ከዚህም በላይ ሊወቀሱ ይገባል ባይ ናቸው። ጥናቱም ቴአትር በአራት ባህሪያት ብቻ ማተኮሩ የኢትዮጵያ ቴአትር በተለይም ኢትዮጵያዊያንን በማሰባሰብ የነበረውን አገልግሎትና ፋይዳ የዘነጋ እንደሆነ ገልጸዋል። ቴአትር በመንግስት ብቻ መታጠሩም ሌላው የተቸካይነት ባህሪ በመሆኑ መንግስት ከቴአትር ላይ እጁን ማንሳት እንዳለበት ይልቁንም ከመንግስት ፍላጎት ማስፈጸሚያነት ወጥቶ ለግል ዘርፍም ሊተውለት እንደሚገባ ሀሳቦችን ሰንዝረዋል።
የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኅላፊ ዶክትር ሂሩት ካሳው የኢትዮጵያ ምድረ ቀደምትነት አንዱ ማስመስከሪያ የራሷ ጥበብ ባለቤት መሆኗን ገልፀው፤ ከ100 ዓመት በፊት ከተጀመረው ዘመናዊ ቴአትር ይልቅ የቅዱስ ያሬድ ዜማ ስልቶች 1 ሺህ 500 ዓመታት ማስቆጠሩን አንስተዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ የጥበብ ምንጭ ናት ይላሉ። ዳሩ ይህ ጥበብ ማደግና መጎልበት የሚችለው ሲኮተኮት ነው ይላሉ። ሂስ ለኪነ ጥበብ ዕድገት ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቴአትር ዕድገት ላይ የተደረገው ሂስም በዚህ ዓመት የተደረገ የመጀመሪያው መድረክ እንደሆነ ገልፀዋል። በቀጣይም ኪነ ጥበቡ ለአገር የሚኖረው ፋይዳ እንዲጎለብት፣ ጥበቡም እንዲያድግ እንዲህ አይነት የሂስ ትንተና መድረኮች (የኪነ ጥበብ ኩትኮታዎች) ይጠናከራሉ ብለዋል።
ምክትል ቢሮ ሃላፊው ሰርፀ ፍሬስብሐት በበኩላቸው ስነ ጥብበ ዕድገትና ልማት ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸው፤ በዚህ የተቋማዊ አደረጃጀት ለውጦች ስለመደረጋቸው አንስተዋል። ያለ ሂስ የደረስንበትን የኪነ ጥበብ ልክ ማወቅ እንደማይቻል ገልጸው፤ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በዕውቀት ላይ የተመሰረቱ የሂስ መድረኮች ቀጣይነት እንደሚኖራቸው አረጋግጠዋል።