ቀጥታ፡

የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ምርመራ በስማ በለው እንዴት ይቻላል?

ኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጻሚችን ተጠያቂ ለማድረግ በመንግስት በኩል የማያወላዳ አቋም መኖሩን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጨ ጉዳይ ሚኒስተር አቶ ደመቀ መኮንን ሰሞኑን አስታውቀዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ይህን ሀሳብ የገለጹት የአውሮፓ ህብረት የዓለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ጁታ ዩራፕሌኒን እና የህብረቱ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካይ ዶ/ር አኔቲ ዌበርን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት ነው።

እርሳቸው እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን በተመለከተ ምርመራም በጠቅላይ አቃቤ ህግ እንዲሁም ከአለም አቀፍ ተቋም ጋር በጥምር ምርመራ አድርጋለች። በዚህ ምርመራ በሚገኘው ውጤት መሰረት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጻሚችን ተጠያቂ ለማድረግ በመንግስት በኩል የማያወላዳ አቋም መኖሩን አረጋግጠዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንዳንድ ዓለም አቀፍ ተቋማትና መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያ ላይ የተዛቡ መረጃዎችን በማውጣት የዓለም ማህበረሰብ የተሳሳተ መረጃ እነዲኖረው የማድረግ ስራዎች እየፈጸሙ ነው።

በተለይ በአንድ ወገን ያደላ መረጃ በማሰባሰብና በማሰራጨት የህግ ማስከበር ሂደቱን የተሳሳተ ምስል እየሰጡት ይገኛል። በተለይም ህግን በማስከበር ሂደት የተከሰቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መኖራቸውን በማመላከት የኢትዮጵያን መንግሰት ተጠያቂ ለማደረግ ብዙ እርቀት እየተኬደ መሆኑን በተለያየ መልኩ የሚወጡ መረጃዎቸ ያረጋግጣሉ።

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ከአገሩ አልፎ ለመላው አፍሪካውያንም ህይወቱን በመስጠት ለህዝቦች ሰላም ዘብ በመቆም በሚታወቀው የአገራችን የመከላከያ ሰራዊት ላይ አሳዛኝና፣ ፈፅሞ የማይገመት ዘግናኝ ጭፍጨፋ የደረሰበት ዕለት ነው።

ይህን እውነትና የጭካኔ ጥግ የተፈጸመበትን ድርጊት ግን አንዳንድ ዓለም አቀፍ ተቋማትና መገናኛ ብዙሃን ምንም እንዳልሆነ ሲያልፉት ተስተውሏል።

በዚህ ዕለት አሸባሪው የህወሃት በአገር መከላከያ ሰራዊት በተለይም በሰሜን ዕዝ ላይ ከፍተኛ የክህደት ጥቃት በመፈጸሙ መንግስት ወደ ህግ ማስከበር ተግባር እንዲገባ ተገዷል። በዚህም በትግራይ ክልል በጀመረው የህግ ማስከበር እርምጃ በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ የክህደት ጥቃትን የመሩ፣ ያስተባበሩና የፈጸሙ በርካታ የአሸባሪው ህወሃት ወንጀለኛ አመራር አባላት የነበሩ በቁጥጥር ስር በማዋል ወደ ህግ እንዲቀርቡ አድርጓል።

አሸባሪው ህወሃት በአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመው የክህደት ጥቃትና እርሱን አስታኮ ያደረጋቸው አስከፊ ድርጊቶችን በጥንቃቄ ሳያዩና ሳይፈትሹ የተለያዩ ዘገባዎች ያወጡ ሪፖርት ያቀረቡ ዓለምአቀፍ መገናኛ ብዙሃንና ዓለም አቀፍ ተቋማት በርካታ ናቸው።

ብዙዎቹ የአገር መከላከያ ሰራዊት ሙሉ ለሙሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደፈጸመ በመግለጽ የዓለምን ማህበረሰብ የማሳሳት ዘማቻ ሲያከናውኑ ቆይተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የዚህ ዓይነቱ የተዛባ መረጃ እንዲስተካከልና ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ የኢትዮጵያን ግልጽ አቋም እንዲረዳ ለማድረግ “ተፈጽመዋል” የተባሉ የሰብዓዊ ጥሰቶች እንዲወጡና ጥሰቱን የፈጸሙ ግለሰቦችም ለፍርድ እንዲቀርቡ ለማድረግ ቁርጠኝነቷን ያሳየችው አፍሪካውያን ተቋማት ጉዳዩን እንዲያጠኑት እድል በመስጠት ነው።

ለዚህ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የካቲት 30 ቀን 2013 ዓ.ም በተካሄደው የአፍሪካ ሰላምና ደህንነት ምክር ቤት ጉባኤ ባደረጉት ንግግር፤ የአፍረካ የሰብዓዊና ህዝቦች መብቶች ኮሚሽን ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጋር በቅንጅት በመሆን ‘ተፈጸሙ’ ተብለው የሚነገሩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መመርመር እንደሚችሉ ይፋ አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ይህን ይፋ ያደረጉት በወቅቱ ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ እንዲበጅ ጽኑ አቋም እንዳላቸው አጽንኦት በመስጠት ነው።

በተጨማሪ መጋቢት 2 ቀን 2013 ዓ.ም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽነር ሙሳ ፋኪ ማህመት ጋር በነበራቸው ውይይት በተመሳሳይ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሃሳብ አጽንኦት ሰጥተው አንስተዋል፡፡

ይህን ተከትሎም የአፍሪካ ሰብዓዊና የህዝቦች መብቶች ኮሚሽን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስቀመጡት አግባብ መሰረት ጉዳዩን ሊመረምር ኃላፊነት ወስዶ ወደ ስራ ለመግባት መንቀሳቀሱ ይታወቃል።

ይህም ሆኖ የኢትዮጵያ መንግስት የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በጋራ ተፈጽሟል በተባለው ድርጊቶች ላይ ምርመራ እያደረጉ መሆኑ ታውቋል። የአፍሪካ ሰብዓዊና የህዝቦች መብቶች ኮሚሽንስ የት ደረሰ? ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጋር እንዲያደርግ የተጋበዘበት ጉዳይ ምን አደረሰው? በዚህ ጉዳይ ላይ መረጃ ያደረሱን የውስጥ ምንጮች እንደሚሉት፤ የአፍሪካ የሰብዓዊና ህዝቦች መብቶች ኮሚሽን ከኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጋር በቅንጅት የመስራቱን ጉዳይ ወደ ጎን በመተው ስራዎችን በተናጥልና ራሱ በፈለገው መንገድ ሲያከናውን ቆይቷል፡፡

ይህ አካሄድ የኢትዮጵያ መንግስት በሁለቱ ኮሚሽን ጉዳዩ እንዲመረመር ያስቀመጠውን አቅጣጫ የሳተ ነው። ድርጊቱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ከመጻረሩ ባለፈ የኮሚሽኑን የሰብዓዊ መብት ምርመራ ቻርተር ድንጋጌዎች የሚጥስ ነው። የኮሚሽኑ ቻርተር አንቀጽ (46) እራሱ በፈለገው መንገድ እና አግባብ ብቻ በአንድ አገር ላይ የሰብዓዊ ጥሰት ምርመራ ማድረግ እንደማይችል ይደነግጋል፡፡

ኮሚሽኑ ስራውን ሲያከናውን ከመሰል የአህጉሪቱና ዓለም አቀፍ ተቋማት እንዲሁም ጉዳዩ ከሚለከተው አገር የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጋር በቅንጅትና በትብብር መስራት እንደሚጠበቅበትም እንዲሁ፡፡ በቻርተሩ መሰረት ኮሚሽኑ ምርመራውን ለማካሄድ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጋር በቅንጅት ለመስራትም እና ሌሎች መስራት የማያስችሉ እንቅፋቶች ሲገጥሙት ለህብረቱ ሰላምና ደህንነት ጉባኤ የማቅረብ ግዴታ አለበት፡፡ ምንጮቻችን እንደገለጹት፤ ኮሚሽኑ ከኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር በትብብር ለመስራትም ፍላጎት ካላማሳየቱም በላይ በተናጠል ሲሰራ ቆይቷል። በትብብር መስራት የማያስችሉ እንቅፋቶች እንዳጋጠሙትም ለጉባኤው አላቀረበም።

ይህ ማለት ደግሞ ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል ተፈጽሟል የተባሉትን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ብቻውን ምርመራውን ራሱ በፈለገው አግባብ ሲያከናውን መቆየቱን ያመለክታል።

የሰብዓዊ መብት ህግ ባለሙያውና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ህብረት ዋና ዳይሬክተር አቶ መሱድ ገበየሁ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በትግራይ ክልል ‘ተፈጸመ’ የተባለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተለያዩ ጊዜያት ለመመርመር የሰሩና እየሰሩ ያሉ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ተቋማት ከሚታይባቸው ዋነኞቹ ችግሮች መካከል ከሀገር አቀፍ መሰል ተቋማት ጋር በትብብር ለመሰራት ፍላጎት ያለማሳየታቸው ነው። ይህ ደግሞ ብቻቸውን በመፈተሽ ለአንድ ወገን ያደላ ውሳኔ ላይ በመድረስ ለዓለም ማህበረሰብ የተዛባ መረጃ እንዲያስተላልፉ እድል ይሰጣል።

የዚህ ዓይነቱ ድርጊት የሚፈጸመው ከመጀመሪያውኑ በህግ፣ በደንብና ራሳቸው ባሰቀመጡት መመሪያ ተገዥ አለመሆን ነው። የኢትዮጵያ መንግስት “የአፍሪካን ጉዳይ በአፍሪካውያን” በሚለው አቋሙ ለአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን በገባው ቃል መሰረት ኮሚሽኑ ጥናት ያለማድረጉ ተገቢነት የጎደለው ድርጊት ብቻ ሳይሆን፤ የአገሪቱንም ሉዓላዊነትን ወደ ጎን የገፋ ነው፡፡

በዚህ ጉዳይ የኮሚሽኑ የምርመራ አካሄድም ሆነ ምርመራ ውጤት ላይ ከወዲሁ የህግና ፖለቲካ ጥያቄዎች እንዲነሳ ማድረጉ አይቀርም። ከምንጮቻችን ባገኘነው መረጃ መሰረት፤ ኮሚሽኑ መረጃ ያሰባሰበበት ሂደት በኮሚሽኑን ቻርተር የተቀመጡ ድንጋጌዎችን የጣሰም ነው፡፡

የኮሚሽኑ ቻርተር አንቀጽ (46) በግልጽ እንደሚያስቀምጠው ኮሚሽኑ የሰብዓዊ ጥሰት ምርመራ ሲያካሂድ የመጀመሪያ ደረጃ መረጃዎችን ማሰባሰብ፣ ሁሉንም ባለጉዳዮች ሚዛናዊ በሆነ አግባብ ማነጋጋር፣ የመስክ ምልከታዎችን ማካሄድ እና ሌሎች የመጀመሪያ ደረጃ መረጃ ማሰባሰብ ሂደቶችን መከተል እንዳለበት ይደነግጋል፡፡

ነገሩ ከዚህ አኳያ ከታየና ከኢትዮጵያ በኩል በትብብር አብሮት የሚሰራ አካል ከሌለ ሊሆን የሚችለው በሌላ ወገን በሚቀርብለት መረጃ ላይ ተንተርሶ መስራት ነው። ከምንጮች ያገኘነው መረጃ የሚያረጋግጠው በትግራይ ክልል ‘ተፈጽሟል’ የተባለውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ለመመርመር በአመዛኙ የ‘ቨርችዋል’ መረጃ አሰባሰብ ስርዓትን የተከተለ መሆኑን ነው። በተጨማሪም የመስክ ምልከታውንም በሱዳን ስደተኞች ካምፕ በሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች ላይ ብቻ ማድረጉን ነው ምንጮቻችን የገለጹልን፡፡

ታዲያ በዚህ መልኩ በተሰበሰበ መረጃ የሚወጣው ውጤት ምንም ሊሆን ይችላል? እጅግ አጠያያቂ ጉዳይ ይሆናል። የዚህ ዓይነቱ አሰራር በተመለከተ የሰብዓዊ መብቶች ህግ ባለሙያው አቶ መሱድ እንደሚሉት፤ የተቋማቱ ከምርመራ ሂደትና የመረጃ ማሰባሰብ ዘዴ ተቀባይነትና ትክክለኛነት ላይ ጥርጣሬ ከተፈጠረ የሚወጣው ሪፖርትም ህጋዊነት አጠያያቂ ይሆናል።

በተለይ በማህበራዊ ሚዲያና በሌሎች የማህበራዊ ትስስር ገጾች በኢትዮጵያ ላይ የተቀናጀና ድራማ በሚመሰል መልኩ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መኖሩን የሚያሳይ ዘመቻ በስፋት በሚከናወንበት ወቅት በአንድ ወገን ላይ የተመሰረተ መረጃና የተቀናበረ ማስረጃ አሰባስቦ ለሪፖርት ማዘጋጀት ተጠያቂነት ያስነሳል። የሰብዓዊ መብት ጥሰትን የተመለከቱ መረጃዎችና ማስረጃዎች የሚሰበሰቡት የመጀመሪያ ደረጃ መረጃ መሰብሰብ የሚጠበቅ ተግባር መሆኑ ይገልጻሉ፡፡

ከዚህ በተቃራኒው በቨርችዋል ዘዴ የሚደረግ መረጃ ማሰባሰብ ውጤቱ በመገናኛ ብዙሃን ዘመቻ እንዲጠለፍ የማድረግ እድሉም ሰፊ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡ “በርቀት ላይ ሆኖ በሚደረግ ምርመራ የሚገኝ ውጤት እንዴት ተዓማኒ ይሆናል?” ሲሉ የሚጠይቁት ባለሙያው አቶ መሱድ፤ በዚህ ሂደት የሚገኝ ውጤቱ መሬት ላይ ያለውን ሃቅ ከማሳየት ይልቅ የመገናኛ ብዙሃን የሀሰት ዘመቻዎች ፍሬ ከመሆን አያልፍም የሚል እምነት አላቸው።

በተጨማሪ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት በአፋርና አማራ ክልል እየተፈጸሙ ያሉ ከባድ የሰብዓዊ መበት ጥሰቶችን ከወዲሁ እንዳላዩ ማለፍ እና ለመመርመርም ፈቃደኝነታቸውን አለማሳየታቸው በትግራይ ክልል ሲያካሄዱት የነበረው የምርመራ ወጤት ፖለቲካዊ ትርጉም እንደሚኖረው አመላካች መሆኑንም ነው አጽንኦት የሚሰጡት።

በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግስት የሰብዓዊ መብት ተቋማት የምርመራ ሂደትን በተገቢው መልኩ መከታታልና የአካሄድ ስህተት ካለም እንዲያስተካከል በዲፕሎማሲያዊ አግባብ መሞገት እንዳለበት ነው የሚያሳስቡት። ይህ ከሆነ የአፍሪካ የሰብዓዊና የህዝቦች መብቶች ኮሚሽን በህጋዊ መንገድ አገር ውስጥ ሳይገባ፣ በትብብር መስራት ካለበት ተቋመ ጋር ሳይሰራ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን የመሰለ ምርመራ ሊያደርግ ይችላል? ጥያቄው የሁላችንም ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም