የብሄራዊ መረጃና ደኀንነት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የደቡብ ሱዳን የመረጃ ኦፊሰሮችን አስመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
የብሄራዊ መረጃና ደኀንነት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የደቡብ ሱዳን የመረጃ ኦፊሰሮችን አስመረቀ
ጥቅምት 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) የብሄራዊ መረጃና ደኀንነት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የደቡብ ሱዳን የመረጃ ኦፊሰሮችን ለመጀመሪያ ጊዜ በመረጃ ኪነሙያ በማሰልጠን በዛሬው ዕለት አስመረቀ።
አገልግሎቱ የሃገርን ብሄራዊ ጥቅም የማስጠበቅ እንዲሁም የህዝብን ሰላምና ደህንነት የማረጋገጥ ተልዕኮውን ከመወጣት ጎን ለጎን በስሩ በሚገኘው የብሄራዊ መረጃና ደኀንነት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በተለያየ ጊዜ ኦፊሰሮችን በመረጃ ኪነ ሙያ በማስመረቅ አሰማርቷል፡፡
ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ በዘርፉ የካበተ ልምዱን ወደ ጎረቤት ሀገር በማሻገር ከደቡብ ሱዳን አቻ የመረጃና ደኀንነት ተቋም ከሆነው ናሽናል ሴኩሪቲ ሰርቪስ የመረጃ ኦፊሰሮችን በመጀመሪያ ዙር ተቀብሎ አሰልጥኗል።
የአገልግሎቱ ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ በምረቃ ስነሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ የደቡብ ሱዳን የመረጃ ኦፊሰሮችን አሰልጥኖ ማስመረቁ በኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን መካከል ያለውን አጋርነትና ትብብር ይበልጥ ያጠናክራል።
ሁለቱ ሀገራት ረጅም አመታት ያስቆጠረ ታሪካዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው መሆናቸውን ያስታወሱት አቶ ተመስገን፤ ደቡብ ሱዳን ነጻነቷን እንድታገኝ ኢትዮጵያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቷን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያና በደቡብ ሱዳን መካከል ያለው ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በሁለቱ ሀገራት የመረጃና ፀጥታ ተቋማት የአጋርነት ስራዎችም ተጠናክሮ መቀጠሉ ቀጣናዊ ደህንነትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን የቀጣናውን ሰላም፣ ፀጥታና ደህንነት ለማስጠበቅ በተቀናጀ ሁኔታ የሚያከናውኗቸው ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አቶ ተመስገን አያይዘው ገልጸዋል።
የዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ፕሬዚዳንት አቶ ወንድወሰን ካሳ በበኩላቸው ለደቡብ ሱዳን የመረጃ ኦፊሰሮች የተሰጠው ስልጠና የደቡብ ሱዳንን ነባራዊ ሁኔታ እንዳገናዘበ ገልጸው፤ በንድፈ ሃሳብና በተግባርም የተደገፈ መሆኑን ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ተመሳሳይ ሥልጠና እንዲሰጥ ከተለያዩ ጎረቤት ሀገራት ጥያቄ እየቀረበለት መሆኑን ጠቁመው፤ የአሁኑ ስልጠና በቀጣናው የመረጃና ደህንነት የልህቀት ማዕከል ለመሆን የያዘውን ራዕይ ለማሳካት እየሰራ መሆኑን እንደሚያመላክት ገልጸዋል።
የደቡብ ሱዳን ናሽናል ሴኩሪቲ ሰርቪስ ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ልዊስ ናታሊ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን መንግሥት ስትራቴጂክ አጋር መሆኗን ገልፀዋል፡፡
ወንድም የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ የረጅም ዓመታት ድጋፍ ባይታከል ደቡብ ሱዳን አሁን ለምትገኝበት ደረጃ የማትደርስ መሆኑን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን የደኀንነትና መረጃ ተቋማቶች የሚያደርጉት የመረጃ ልውውጥ እየተጠናከረ መምጣቱን የገለጹት ጀነራል ናታሊ፤ ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን የመረጃ ኦፈሰሮች እየሰጠች ያለው ሥልጠናም እየተፈጠረ ያለውን ግንኙነት ይበልጥ እንደሚያጠናክርና በቀጠናውም የሚኖረውን የደህንነት ስጋት ለመቅረፍ እገዛ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን የደኀንነትና የመረጃ ተቋማት ትብብር እየተጠናከር በመምጣቱ ምክንያት በሁለቱ ሀገራት ድንበር አካባቢ ጠንካራ የመረጃ ልውውጥ በማድረግ ሽብርተኝነት፣ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችንና ህገ ወጥ ድርጊቶችን በመከላከል ረገድ የተቀናጁ ሥራዎችን እየተሰሩ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ጀምስ ሞርጋን በኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን መካከል ያለውን ዘርፈ ብዙ ግንኙነትና ትስስር ይበልጥ ለማስቀጠል በተለያዩ መንገዶች ሥራዎች እየተከናወኑ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን የነጻነት ትግል ውጤት እንዲያስገኝ ዘርፈብዙ ድጋፎችን ስታደርግ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ከነጻነት ወዲህም ባሉት ሂደቶች በሁለቱ ሀገራት መካከል ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተመሰረተ ሲሆን፤ በጋራ የፀጥታ ጉዳዮች፣ በባህል፣ በኢኮኖሚና በሌሎችም ዘርፎች ያለውን ግንኙነት ለማሳደግ የተለያዩ ስምምነቶች እንድተካሄዱ መግለፃቸውን የብሄራዊ መረጃና ደኀንነት አገልግሎት ለኢዜአ በላከው መረጃ አመልክቷል፡፡