ወቅታዊ እና ትክክለኛ መረጃ በማድረስ በመረጃ የበለጸገ ማኅበረሰብ ለመፍጠር እንሰራለን - ኢዜአ አማርኛ
ወቅታዊ እና ትክክለኛ መረጃ በማድረስ በመረጃ የበለጸገ ማኅበረሰብ ለመፍጠር እንሰራለን
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) ወቅታዊ እና ትክክለኛ መረጃዎችን በማድረስ በመረጃ የበለጸገ ማኅበረሰብ ለመፍጠር እንደሚሰራ የአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ገለጸ፡፡
ከመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ጋር በቅንጅት ለመስራት የተወያየው ቢሮው ነዋሪዎችን በተለያዩ ዘርፎች ተጠቃሚ ለማድረግ የሚከናወኑ ተግባራትን ተደራሽ በማድረግ ረገድ በጋራ እንደሚሰራ ተገልጿል።
የቢሮው ሃላፊ አቶ ዮናስ ዘውዴ የሠላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ውጥኖችን እውን በማድረግ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለማየት የመገናኛ ብዙሃን ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።
መገናኛ ብዙሃን ይህን ሚናቸውን እንዲወጡም በአዲስ መልክ የተደራጀው ቢሮው በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊና በሌሎች ጉዳዮች የተደራጀ መረጃ ለማቅረብ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።
በተቋማት መካከል ባልተደራጀ መንገድ እየተካሄደ ያለውን የመረጃ ፍሰት በማስተካከል ለማሳለጥ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
ቢሮው ከመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ጋር ተቀናጅቶ በመረጃ የበለጸገ ማኅበረሰብ በመፍጠር የአገር ግንባታ ሚናውን የሚወጣ መሆኑንም አክለዋል።
በመድረኩ ሃሳባቸውን የሰጡ የመገናኛ ብዙሃን አመራሮች የቢሮው ዳግም መቋቋም መረጃ ለማግኘት የነበረውን እንግልት በማስቀረት መረጃዎችን ከአንድ ቋት እንዲያገኙ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።
ቢሮው ተቋማትን በመመርመር ጉልበት ያለው፣ ሃቀኛ እና ለከተማዋ ነዋሪዎች የሚመጥን ጠንካራ መረጃ ማቅረብ እንዳለበትም ጠቁመዋል።
በአገልግሎት አሰጣጥ ሂደት የማኅበረሰቡን ችግሮች አውጥቶ በማሳየት መፍትሄ የሚገኝበትን አሰራር ዘርግቶ ተጠቃሚ እንዲያደርግም አሳስበዋል፡፡
የመዲናዋን ገጽታ ማሳየት የሚችል ለአገር ውስጥ ነዋሪዎችና ለዓለም አቀፉም ማኅበረሰብ መረጃ መስጠት የሚችል ድረ ገጽ ማበልጸግ እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡
በውይይቱ የማጠቃለያ ሃሳብ የሰጡት የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ዋቻሞ ጴጥሮስ ቢሮው በአገሪቷ ሚዲያ ያለውን የመረጃ ጥም ለማሟላት በትጋት ይሰራል ብለዋል፡፡
ቢሮው የከተማ አስተዳደሩን ትክክለኛና ተዓማኒ መረጃዎች ለመገናኛ ብዙሃን በመስጠት ግንባር ቀደም እንደሚሆንም ተናግረዋል።