ቀጥታ፡

የአሸባሪውን ህወሃት ኢትዮጵያን የመበተን ህልም በማክሸፋ ለዜጎቻችን እፎይታን የምንቸርበት ጊዜ ሩቅ አይደለም

ጥቅምት 18/2014 (ኢዜአ) "የአሸባሪውን ህወሃት ኢትዮጵያን የመበተን ህልም በአጠረ ጊዜ በማክሸፍ ለዜጎቻችን እፎይታን የምንቸርበት ጊዜ ሩቅ አይደለም" ሲሉ ወሎ ግንባር የተገኙ የጎንደር ፋኖ አባላት ተናገሩ።

አሸባሪው ህወሃት በአፋርና በአማር ክልል ወራራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች በሰው ልጆች ይደረጋሉና ይታሰባሉ ተብለው የማይገመቱ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶችን ፈፅሟል።

ለዜጎች ማህበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ አገልግሎት የሚሰጡ ትምህርት ቤቶች፣ ጤና ተቋማት፣ ቤተ እምነቶች እና ሌሎች የአገር ሃብቶች ላይ የከፋ ጉዳት አድርሷል።

ክቡር የሆነውን የሰው ልጅም ገሎ በጅብ በማስበላት ፣ ታዳጊ ህፃናትን በመድፈር ለከባድ የስነ ልቦና ጉዳት ሰለባ በመዳረግና፣ በርካታ ንጹኃን ዜጎችን ከሞቀ ጎጇቸው በማፈናቀል ለከፋ ማህበራዊና ሰብዓዊ ቀውስ እንዲጋለጡ ምክንያት ሆኗል።

አሸባሪው ቡድን የወረራ አድማሱን ለማስፋት ካለው ጽኑ ፍላጎት የተነሳ በተለመደ ቅጥፈቱ የደሴና ኮምቦልቻ ከተሞችን ተቆጣጥሪያለሁ፤ ጦርነቱም አልቋል በማለት በከንቱ ምኞት እየናወዘ ነው፡፡

ሃቁ ግን የወራሪው የጥፋት ፕሮፕጋንዳ በጀግኖች የሰራዊት አባላት መክሰሙና የጥፋት እግሮቹም ላይንቀሳቀሱ መሽመድመዳቸው ነው።

የህልውናውን ዘመቻው በድል ለማጠናቀቅ ከጎንደር ተነስተው ወደ ወሎ ግንባር የተመሙት ፋኖዎች "ኢትዮጵያን ክዶ ህዝቦቿን ለከፋ ስቃይ እየዳረገ የሚገኘውን ወራሪ ኃይል ለማጥፋት በቆራጥነት ተነስተናል" ብለዋል።

ናሁሰናይ አንዳርጌ "ኢትዮጵያን ለዳግም ብዝበዛ የዳረጋትን ወራሪ ኃይል ለማጥፋት በፅናት እንፋለማለን" ብሏል።

"እናቶቻችንና እህቶቻችንን በመድፈር ፣ ዜጎችን በማፈናቀል እና በመዝረፍ ለከፋ ሰብዓዊ ቀውስ የዳረገውን ወራሪ ኃይልም እንዳመጣጡ ለመመከት ተዘጋጅተናል" ሲል ነው ያከለው።

አሸናፊ ይሁኔ እንዲሁ በአገር ክህደት ላይ የሚታወቀውን ወራሪ ኃይል ግብዓተ መሬት በመፈጸም "ኢትዮጵያን ለማዳን ማንኛውንም አይነት አማራጭ እንወስዳለን" ሲል አረጋግጧል።

የወራሪውን ኃይል የጥፋት መንገድ ማክሰም ለሰራዊቱ ብቻ የሚተው ባለመሆኑ፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የጀመረውን የትጥቅና ስንቅ ድጋፍ አጠናክሮ እንዲያስቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

በጦርነት ቀጣና የሚገኘው የወሎ ህዝብም በሌሎች የጦርነት ቀጣና የተሰሩ ውጤታማ የደጀንነነት ስራዎችን በግንባሩ መድገም እንዳለበት አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም