ቤተክርስቲያኗ በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋ ከቀዬአቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች 50 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ታደርጋለች - ኢዜአ አማርኛ
ቤተክርስቲያኗ በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋ ከቀዬአቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች 50 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ታደርጋለች
ጥቅምት 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋ ከቀዬአቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች 50 ሚሊዮን ብር ድጋፍ እንደምታደርግ የቤተክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ አስታወቀ፡፡
የቤተክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ ለአንድ ሳምንት ሲያካሒድ የነበረውን ዓመታዊ ጉባኤ መጠናቀቅ አስመልክቶ መግለጫውን በንባብ አሰምቷል፡፡
ሲኖዶሱ በዚህ ወቅት በሀገሪቱ በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋ ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች 50 ሚሊዮን ብር ደጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡
በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት በሀገር ውስጥ የተከሰተውን ግጭት ምክንያት በማድረግ አንዳንድ ግለሰቦች ሕዝብን ከሕዝብ ለመነጠል የሚያከናውኑትን ተግባር በፅኑ እንደሚያወግዝም ነው የገለጸው፡፡
ኢትዮጵያውያን ለሀገር ሰላምና አንድነት በትብብር እንዲሰሩም ሲኖዶሱ ጠይቋል።
ሲኖዶሱ በመግለጫው በውጭ ሀገር የሚገኙ አንዳንድ ካሕናት ከቤተክርስቲያን አገልጋዮች በማይጠበቅ መልኩ የሕዝብን አንድነት የሚሸረሽር ቅስቀሳ እያደረጉ መሆኑን አስታውቆ፤ እነዚህ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ጠይቋል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶሱ እነዚህ አካላት ወደ ሰላምና አንድነት እንዲመለሱ የሚሰራና የሚያስተባብር የሰላም ልዑክ እንዲቋቋም መወሰኑንም ጠቁሟል።
ኢትዮጵያውያን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ቅዱስ ሲኖዶሱ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶሱ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ነጻና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በስኬት በመከናወኑ ቤተክርስቲያኗ ደስታ እንደተሰማት አስታውቆ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የተሳካ የኃላፊነት ጊዜ እንዲገጥማቸው መልካም ምኞቱን ገልጿል።
ቅዱስ ሲኖዶሱ ለአንድ ሳምንት ሲያካሄድ በቆየው ዓመታዊ ጉባኤ የአብነት ትምሕርት ቤቶች፣ የስብከተ ወንጌል መስፋፋት፣ የሰንበት ትምህርት ቤቶች መጠናከርን ጨምሮ ሀገራዊ ሰላምና አንድነት ላይ ሰፊ ውይይት ማድረጉን አመልክቷል።