ቀጥታ፡

አሸባሪው ህወሃትን ለማጥፋት ተጋድሎ እያደረገ ለሚገኘው ሰራዊት ደጀንነታቸውን አጠናክረው ይቀጥላሉ

አዲስ አበባ ጥቅምት 18/2014 (ኢዜአ)"መደበኛ ስራችንን እያከናወን ወራሪውን የህወሃት ሽብርተኛ ኃይል ለማጥፋት ተጋድሎ እያደረገ ለሚገኘው ሰራዊት ደጀንነታችን እናስቀጥላለን" ሲሉ የደሴ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
የደሴ ከተማ ነዋሪዎች ለኢዜአ ሪፖርተሮች እንደገለጹት፤ ከመደበኛ ስራቸው ጎን ለጎን የአሸባሪውን የህወሃት ኃይል ለመደምሰስ ለተሰለፈው ሰራዊት የሚያደርጉትን ደጀንነት በስፋት ቀጥለዋል።

የከተማዋን ማህበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ ለመታዘብ ኢዜአ በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች ምልከታ አድርጓል።

በዚህም የከተማዋ ነዋሪዎች በአሸባሪው ህወሃት የሃሰት ወሬዎች ሳይረበሹ መደበኛ እንቅስቃሴቸውን በማሳለጥ ላይ መሆናቸውን ተመልክቷል።

በከተማዋ የሚገኙ የግል ንግድ ድርጅቶች የመንግስት ማህበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ትራንስፖርት እና ሌሎች የግብይት ቦታዎች መደበኛ ስራዎቻቸውን በማስኬድ ላይ እንደሚገኙ ማረጋገጥ ተችሏል።

ሃሳባቸውን ያካፈሉን የከተማዋ ነዋሪዎች የደሴ ከተማ ልክ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማህበራዊ ኩነቶችን በማካሄድ ላይ ለመሆኗ ማሳያ ናቸው።

መደበኛ ስራዎቻቸውን በማከናወንም ወራሪውን የአሸባሪው ህወሃት ሃይልን በመፋለም ላይ ለሚገኘው ሰራዊት ደጀንነታቸውን እያስቀጠሉ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

በደሴ ከተማ በተለምዶ ፒያሳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ፋጤ ሰይድ እና ወይዘሮ አሚናት መላኩ "የደሴ ከተማ ጠላት ተመኝቶ እንዳስወራላት ሳይሆን ልክ እንደከዚህ ቀደሙ መደበኛ ስራዋን እያስኬደች" መሆኗን ተናግረዋል።

የአሸባሪው ሕወሃት ቡድኑ ሰርጎ ገብ የጥፋት መልዕክተኞች በመከታተልና ቁጥጥር በማድረግ ለህግ ለማቅረብ መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።

አካባቢያቸውን በንቃት በመጠበቅ ወራሪውን ኃይል ፊት ለፊት እየተፋለመ ለሚገኘው ሰራዊት የሚያደርጉትን ደጀንነት እያስቀጠሉ ስለመሆኑ አረጋግጠዋል።

አቶ አዎል ዩሱፍ እና ወጣት ሰለሞን ጋሻው የተባሉት የደሴ ነዋሪዎች በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ለአሸባሪው ህወሃት የሽብር ወሬ ጆሮ መስጠት አያስፈልግም፡፡

በተለይ ወጣቱ ግንባር ድረስ በመሄድ የአሸባሪው ህወሃት ለማጥፋት ፍልሚያ ላይ ለሚገኘውን ሰራዊት የትጥቅና ስንቅ ድጋፍ በማድረግ ደጀንነቱን በተግባር እያሳየ ስለመሆኑ አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም