የኢትዮጵያ አቋም የሱዳን ሕዝብ ፍላጎት እንዲሳካ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አቋም የሱዳን ሕዝብ ፍላጎት እንዲሳካ ነው
ጥቅምት 18 / 2014 (ኢዜአ) "የኢትዮጵያ አቋም የሱዳን ሕዝብ ፍላጎት እንዲሳካና በሱዳን የተሳካ ሽግግር እንዲካሄድ ነው" ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ።
አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት፤ በሱዳን በተፈጠረው ወቅታዊ ችግር የኢትዮጵያ መንግሥት ከወንድም የሱዳን ሕዝብ ጎን ቆሟል።
ይህም መልዕክት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል መተላለፉን ጠቁመው፤ ኢትዮጵያ ለሱዳን ሕዝብ አጋርነት ማሳየቷን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያና የሱዳን ሕዝብ የረጅም ጊዜ ወዳጅነት ያላቸው በርካታ የሚያመሳስሏቸው ጉዳዮች መኖራቸውን አንስተው ፍላጎታቸው ተቀራረቢ መሆኑንን ጠቁመዋል።
አሁን ሱዳን ከገጠማት ችግር በራሷ የመውጣት አቅም እንዳላት ገልጸው፤ "በሱዳን የውስጥ ጉዳይ የውጭ ጣልቃ ገብነት አስፈላጊ አለመሆኑን ኢትዮጵያ ታምናለች" ብለዋል።
የሱዳን ሕዝብ ፍላጎት እንዲሳካ የኢትዮጵያ መንግሥት አቋም መሆኑን አምባሳደር ዲና በመግለጫቸው አጽንዖት ሰጥተውታል።
በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ኢትዮጵያ ከሱዳን ሕዝብ ጋር በመቆሟ የኢትዮጵያን የማያወላውል አቋም እንደሚያሳይ ገልጸው፤ "ኢትዮጵያ አጋርነቷን ትቀጥላለች" ብለዋል።
በተለይም የተጀመረው የለውጥና የዴሞክራሲ ሽግግር ሥራዎች ግባቸውን እንዲመቱ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቷን እንደምታጠናክር ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ለበርካታ የአውሮፓ አገራት አምባሳደሮች በወቅታዊ ጉዳይ ማብራሪያ መስጠታቸውን አንስተዋል።
በተመሳሳይ ለአውሮፓ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ዶክተር አኔት ዌበርንና ለተመድ የስደተኞች ጉዳዮች ረዳት ከፍተኛ ኮሚሽነር ራውፍ ማዙም ማብረሪያ ሰጥተዋል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተካሄደውን የለውጥ ሥራ ተከትሎ ኢትዮጵያን በውጭ በሚወክሏት ሚሲዮኖች የሚያገለግሉ ዲፕሎማቶች በቅርቡ የሚደለደሉ መሆኑን አምባሳደር ዲና ጠቁመዋል።
በሳዑዲ አረቢያ በችግር ላይ የሚገኙ ዜጎቻችን ወደ አገራቸው የመመለስ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም በሳምንታዊ መግለጫቸው አብራርተዋል።