የታላቁ ህዳሴ ግድብ ጉዳይን የዘወትር አጀንዳ አድርጎ መስራት ይገባል -ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ጉዳይን የዘወትር አጀንዳ አድርጎ መስራት ይገባል -ምሁራን
ሀዋሳ፤ ጥቅምት 18/2014 (ኢዜአ) ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለውን የታላቁ የህዳሴ ግድብ ጉዳይ የዘወትር አጀንዳ አድርጎ መስራት እንደሚገባ የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ምሁራን አስገነዘቡ።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ዳጋላ ኤርጋኖ ለኢዜአ እንደገለጹት የህዳሴ ግድብ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አሻራውን ያኖረበት ነው።
"ሀገራዊ አጀንዳ የሆነው ግደቡ ህዝቡን በአንድ አስተሳስሮ ያቆመ ታላቅ ፕሮጀክት በመሆኑ ሁሉም ሰው ግንባታው ተጠናቆ ወደ ሥራ የሚገባበትን ጊዜ በጉጉት የሚጠብቀው ነው" ብለዋል ፡፡
ግድቡ ከህዝባዊ ተሳትፎው ባሻገር ከፍተኛ ሙያዊ ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን የጠየቀ ፕሮጀክት መሆኑን ተናግረዋል ፡፡
በዚህ ዓመት የግድቡን ሁለት ተርባይኖች ወደ ሥራ በማስገባት ኃይል ማመንጨት ይጀምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ያስታወሱት ዶክተር ዳጋላ የግደቡ ሀይል ማመንጨት መጀመር የአፍሪካ ቀንድን መልካ ምድራዊ የፖለቲካ ሁኔታዎችን የሚቀይርና ምጣኔ ሀብታዊ ጥቅም የሚያስገኝ መሆኑን አስረድተዋል።
ለኢንዱስትሪው ዘርፉ ትልቅ አቅም በመፍጠር ኢትዮጵያ ከግብርና ጥገኝነት የተላቀቀ ኢኮኖሚ ለመገንባት የምታደርገውን ጥረት እንደሚደግፍ ገልፀዋል ፡፡
በሀገር ውስጥ የኃይል ፍጆታን ከማሟላትና የነዳጅ ኃይል ወጪን ከመቀነስ ባሻገር ተጨማሪ የውጪ ምንዛሪን እንደሚያስገኝ አመልክተዋል።
የሚፈጠረው አቅም በኢኮኖሚ ጥገኝነት ምክንያት ከሚመጣ የውጭ ጣልቃ ገብነት ኢትዮጵያን የሚታደጋት እንደሆነ ተናግረዋል።
ለግድቡ ፍፃሜ መረባረብ እንደሚገባ ያመለከቱት ምሁሩ ''በተለይ ምሁራን የግድቡን ጠቀሜታና ተያያዥ እውነታዎችን በምርምር በማስደገፍ የሁልጊዜም አጀንዳችን አድርገን ልንሰራ ይገባል'' ብለዋል ፡፡
ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን ባለማስደፈር የአፍሪካዊያን ተምሳሌት እንደሆነች ያስታወሱት ምሁሩ በውጭ ተፅዕኖ የማይወድቅ ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ለመገንባት መረባረብ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በዩኒቨርሲቲው የልማት ጥናትና የጋዜጠኝነት መምህርና ተመራማሪ ዶክተር መልሰው ደጀኔ በበኩላቸው የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ስኬት ኢትዮጵያ የራሷን የተፈጥሮ ሀብት የመጠቀም ፍላጎት የማይቀለበስበት ደረጃ መድረሱን የሚያመለክት መሆኑን ተናገረዋል።
''ሀገር በህልውና ዘመቻ ላይ ብትሆንም የህዳሴው ግድብ ሥራ ለአፍታም ሳይቋረጥ ቀጥሏል'' ያሉት ዶክተር መልሰው የግድቡ ግንባታ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት እስከሚውል በፕሮጀክቱ ዙሪያ መዘናጋት እንደማያስፈልግ አመልክተዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ በሚደረገው ጦርነት ውስጥ እጃቸውን ለማስገባት የሚጥሩ ሀገራት የግድቡን ሥራ ለማደናቀፍ አጀንዳ ቀርፀው እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል ፡፡
ከህልውና ዘመቻው ጎን ለጎን ግድቡን ለፍፃሜ ማብቃት እንደሚጠበቅ ያመለከቱት ምሁሩ የኢትዮጵን ሀቅ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የማሳወቅ የእለት ተለት ሥራ ከምሁራን አንደሚጠበቅ አመልክተዋል ፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ የውጭ ጣልቃ ገብነትን የሚያስቀርና ከኢኮኖሚ ጥገኝነት የሚያላቅቅ በመሆኑ ለፍጻሜው ስኬት የዘወትር አጀንዳ አድርጎ መስራት እንደሚገባ ምሁራኑ አስገንዝበዋል።