ወጋገን ባንክ ለኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማዕከል አንድ ሚሊዮን ብር ለገሰ - ኢዜአ አማርኛ
ወጋገን ባንክ ለኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማዕከል አንድ ሚሊዮን ብር ለገሰ
አዲስ አበባ ጥቅምት 18/2014 (ኢዘአ) ወጋገን ባንክ 25ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በማስመልከት ለኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማዕከል የአንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ አበረከተ።
የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አብዲሹ ሁሴን የገንዘብ ድጋፉ በልብ ሕመም ለሚሰቃዩ ሕጻናት ሕክምና የራሱ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
ባንኩ በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች ለሚገኙና ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የበኩሉን እገዛ በማድረግ፤ በአገር ልማትና ተያያዥ ጉዳዮች ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት እንደሚሰራም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ማዕከል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ህሩይ አሊ ባንኩ በተለያዩ ጊዜያት ለማዕከሉ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል።
ድጋፉ የብዙ ሕጻናትና ወላጆቻቸውን ችግር ከማቃለሉ ባሻገር ሕይወት የሚታደግ እንደሆነም አክለዋል።
ሌሎች ተቋማትም ይህን ፈለግ በመከተል የሕጻናቱን ሕይወት እንዲታደጉ ጥሪ አቅርበዋል።
የማዕከሉ የበጎ ፍቃድ አምባሳደር አርቲስት መሰረት መብራቴ የኢትዮጵያዊያን መገለጫ የሆነው የመረዳዳትና የመደጋገፍ በጎ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቃለች።