ቀጥታ፡

እየተደረጉ ያሉ ድጋፎች ችግሮቻችንን ታሳቢ ያደረጉ ናቸው

ጥቅምት 18/2014 (ኢዜአ) በድርጅቶችና በህብረተሰቡ እየተደረገላቸው ያለው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ችግሮቻቸውን ታሳቢ ያደረጉ መሆኑን በእብናት መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በህወሓት የሽብር ቡድን ወረራ ምክንያት ከዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ተፈናቅለው በእብናት የመጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ወገኖች ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው ቁሳቁሶችን ድጋፍ አድርጓል።

በመጠለያ ጣቢያው ከሚገኙት ተፈናቃዮች መካከል ወይዘሮ ስንታየሁ መንግስቱ ፤በመጠለያ ጣቢያው ከመስከረም ወር ጀምሮ ህፃን ልጃቸውን ይዘው ተጠልለው እንደሚገኙ ለኢዜአ ተናግረዋል።

ቀይ መስቀልን ጨምሮ የተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ግለሰቦች ለእናቶችና ህፃናት ትኩረት ያደረገ ድጋፍ እያደረጉላቸው መሆኑን አመልክተዋል።

ቀይ መስቀል ካሁን ቀደምም ብርድ ልብስና የማብሰያ ቁሳቁስ ድጋፍ እንዳደረገላቸው ጠቅሰው፤ ከትናንት በስቲያ ደግሞ የማብሰያ እቃዎች፣ አልባሳትና ለህፃን ልጃቸው ንፅህና መጠበቂያ እንደሰጣቸው ገልጸዋል።

የተደረገላቸው ድጋፍም ችግራቸውን ለማቃለል እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል።

ድጋፍ ከመስጠት ጎን ለጎንም መንግስት በአካባቢያቸውን ሰላም አስፍኖ ወደ ቀያቸው መመለስ እንዲችሉ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።

ወይዘሮ ገነት ከፍያለው በበኩላቸው፤አሸባሪው ህወሓት በፈጠረው ጦርነት ምክንያት ይኖሩበት ከነበረው ሰቆጣ ከተማ በመፈናቀል ሁለት ህፃን ልጆቻቸውን ይዘው እብናት መጠለያ ጣቢያ ተጠልለው እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ወደ መጠለያ ጣቢያው ከመጡ ጀምሮ የተለያዩ የምግብና አልባሳት ድጋፎች እየተደረገላቸው መሆኑን ነው ያስረዱት።

ቀይ መስቀል ያደረገላቸው ድጋፍ ልጆችቸውን ከብርድ ከመታደጉም ባለፈ አብስለው ለመጠቀም የሚያስችላቸውን አቅም እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።

የእብናት መጠለያ ጣቢያ የሎጅስቲክ ሃላፊ አቶ መልካሙ ደስታ ፤የአሸባሪው ህወሓት ቡድን በፈፀመው ወረራ በዋግህምራ ዞን የተፈናቀሉ 20 ሺህ ሰዎች በመጠለያ ጣቢያው ተጠልለው እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

የእብናት ወረዳ ነዋሪዎች፣ መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ደርጅቶች እንዲሁም በጎ ፈቃደኛ ግለሰቦች በመጠለያ ጣቢያው ለሚገኙ ወገኖች ያልተቋረጠ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን አስረድተዋል።

ቀይ መስቀል ማህበር ለሴቶች ፣ህፃናት፣አካል ጉዳተኞችና ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች ያሉባቸውን ክፍተት ታሳቢ ባደረገ መልኩ ሁለገብ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በህወሓት የሽብር ቡድን ወረራ ተፈናቅለው በየመጠለያ ጣቢያዎቹ ለሚገኙ ወገኖች ያልተገደበ የሰብአዊ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሻንበል ዋለ ነው።

ለትናንት በስቲያም ከዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ተፈናቅለው እብናት የመጠለያ ጣብያ ለሚገኙ 3 ሺህ ወገኖች ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን ድጋፍ መደረጉን አስታውቀዋል።

ድጋፉ የምግብ ዱቄት፣ ዘይት ፣የሴቶች ንፅህና መጠበቂያ፣አልባሳት ፣ድንኳኖችና የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች መሆናቸውን አብራርተዋል።

በአሸባሪው ወረራ የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ ቀያቸው ተመልሰው እስኪቋቋሙ ድረስ ማህበሩ የሚያደርገውን ያልተገደበ ሰብአዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም