ቀጥታ፡

በደቡብ ክልል አዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ በ161 ትምህርት ቤቶች በሙከራ ደረጃ ይተገበራል

ጥቅምት 17 / 2014 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል አዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ በ161 ትምህርት ቤቶች በሙከራ ደረጃ እንደሚተገበር የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

ፍኖተ ካርታው በመጪው የትምህርት ዘመን በሁሉም ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ እንደሚሆን ተመልክቷል፡፡

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ደረሰ ገቲሳ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በክልሉ ሀገር በቀል ዕውቀት ላይ ትኩረት አድርጎ የተዘጋጀው ፍኖተ ካርታ በሙከራ ደረጃ ይፈተሻል፡፡

ፍኖተ ካርታው ለሙያና ምርታማነት፣ ለሥራ ፈጠራ፣ በሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደትና ህብረ ብሔራዊ አንድነት ለማረጋገጥ አስተዋጽኦ እንዳለው አስረድተዋል፡፡

ሙከራው ባለፈው የትምህርት ዘመን በተለያዩ ቋንቋዎች በተዘጋጁ መጻህፍት በ138 የመጀመሪያና በ23 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደሚተገበርም አስረድተዋል፡፡

ሙከራው በተያዘው የትምህርት ዘመን ክልላዊና ብሔራዊ ፈተና በሚወስዱ በስምንተኛና በ12ኛ ክፍሎች ሙከራ እንደማይደረግበት ምክትል ኃላፊው ገልጸዋል።

ፍኖተ ካርታው የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ዕድገት ስለሚያረጋገግጥ በየደረጃው የሚገኙ የትምህርት አመራሮችና ባለሙያዎች ሙያዊ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የነበረው ሥርዓተ ትምህርት ከውጭ የተቀዳና የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ ነበር ያሉት ደግሞ በሃላባ ዞን ትምህርት መምሪያ የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪ አቶ ጀማል እኒቻ ናቸው፡፡

አዲሱ ፍኖተ ካርታ በይዘቱ ባህል፣ እሴቶችንና ወጎችን ታሳቢ በማድረግ ሀገር በቀል ዕውቀት እንደሚያስጨብጥ ገልጸዋል፡፡ተማሪዎች አካባቢያቸውንና ሀገራቸውን ከማወቅ አልፈው ዓለም አቀፋዊ ግንዛቤያቸውን እንደሚያሳድጉበትም አመልክተዋል፡፡

ፍኖተ ካርታውን ለመተግበር በ"ሃላቢሳ" ቋንቋ ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ክፍል የመማሪያ መጻህፍት መዘጋጀታቸውን ቡድን መሪው አስታውቀዋል፡፡

የወላይታ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ታደሰ ኩማ በበኩላቸው "አሮጌው ሥርዓተ ትምህርት ባሉበት ችግሮች ተማሪዎች በደረጃቸው ማግኘት የሚገባቸውን ዕውቀት እንዳይጨብጡ አድርጓል" ብለዋል።

በአንፃሩ አዲሱ ፍኖተ ካርታ ንድፈ ሃሳብን ከተግባር ጋር እንዲሁም ቴክኖሎጂና ሥራ ፈጠራን አጣምሮ በመያዙ ለሰው ኃይል ልማት አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም