የአዲስ አበባ ዲያስፖራዎች ማህበር ሊመሰረት ነው

39
አዲስ አበባ ነሃሴ12/2010 የአዲስ አበባ ዲያስፖራዎች ማህበር ሊመሰረት ነው። ማህበሩ ዲያስፖራው ወደ ሀገሩ  ሲመጣ የሚገጥሙትን መዋቅራዊ ችግሮች ለመፍታት ከመንግስት ጋር በጋራ እንደሚሰራም ተገልጿል። የማህበሩ ዓላማ ዲያስፖራው በአገሩ የሚያደርገውን ሁለገብ ተሳትፎ እንዲያጠናክር፣ ለሰላምና መግባባት ግንባታ እንዲሳተፍ እንዲሁም በእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ስልጠና እንዲሰጥ መሆኑ ተነግሯል። ማህበሩን ለመመስረት ባለፉት ሶስት ወራት በተቋቋመ ኮሚቴ አማካኝነት የመተዳደሪያ ደንብና የመነሻ ሰነድ መዘጋጀቱ ተገልጿል። የማህበሩ መስራች ኮሚቴ ዛሬ በጠራው ጠቅላላ ጉባኤም በ23 መስራች አባላትና ሰባት የቦርድ አባላት ማህበሩን ሊመሰርት ቢያቅድም የቀረቡት የቦርድ አባላት የተመረጡት በመስራች ኮሚቴው አማካኝነት በመሆኑ እንደገና እንዲታይ ተሳታፊዎች በጠየቁት መሰረት እንዲራዘም ተደርጓል። የቀረቡት እጩ የቦርድ አባላትም በኮሚቴው እንጂ በጠቅላላ ጉባኤው ባለመመረጣቸው ሁሉንም ዲያሰፖራ ይወክላሉ የተባሉ 30 መስራች አባላትን እንደገና በመምረጥና 30ዎቹ ከመካከላቸው የቦርድ አባል የሚሆኑ ሰባት ሰዎችን መርጠው እንዲያቀርቡ በመወሰን ምስረታው ለሌላ ጊዜ ተራዝሟል። በጉባኤው ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ የማህበሩ መመስረት የእውቀትና ቴክኖሎጂን ሽግግር ለማፋጠን እንደሚያግዝ ተናግረዋል። ዲያስፖራው መደራጀቱ የሚገጥሙትን ችግሮች በተቀናጀና በበሰለ መንገድ ለመፍታት እንደሚያስችለውና ከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ እንደሚያደርግለትም ቃል ገብተዋል። ከኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበር በተጨማሪ የኦሮሚያ፣ አማራ፣ ሶማሌ፣ ሀረሪ ክልሎች የዲያስፖራ ማህበራት መመስረታቸው ይታወቃል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም