በሱዳን ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር ኢትዮጵያ የበኩሏን አዎንታዊ አስተዋጽዖ ማድረግ ይጠበቅባታል - ኢዜአ አማርኛ
በሱዳን ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር ኢትዮጵያ የበኩሏን አዎንታዊ አስተዋጽዖ ማድረግ ይጠበቅባታል
ጥቅምት 17/2014/ኢዜአ/ "በሱዳን ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር ኢትዮጵያ የበኩሏን አዎንታዊ አስተዋጽዖ ማድረግ ይጠበቅባታል" ሲሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ የእስያ ጥናት ማዕከል ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተፈራ ተናገሩ።
የሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር ሃሰን አልበሽር ከሁለት ዓመታት በፊት በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን ከወረዱ በኋላ አገሪቷን የሚያስተዳድራት ጥምር መንግሥት መመሥረቱ ይታወቃል።
በወታደራዊ ክንፉ፣በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና በሲቪል ተወካዮች የጋራ ጥምረት የተመሰረተው መንግሥት በሱዳን የዴሞክራሲ ሽግግር እንዲሳለጥ ለሦስት ዓመታት መሰየሙ አይዘነጋም።
ኢትዮጵያ በአደራዳሪነት በተሳተፈችበት በዚሁ የጥምር መንግሥት ምሥረታ አብደላ ሃምዶክን በጠቅላይ ሚኒስትርነት በመሰየም አገሪቷን ከነበረችበት የውስጥ ችግር ለማላቀቅ ሲሰሩ ቆይተዋል።
ሆኖም በአገሪቷ ያለው የፖለቲካና የምጣኔ ኃብት ችግር ሳይፈታ በመዝለቁ ላለፉት ሁለት ዓመታት የታሰበው ለውጥ በሱዳን ሰማይ ሥር አለመታየቱን የተለያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ።
በጥምር መንግሥቱ ውስጥ የሚታዩት አለመግባባቶችና የምጣኔ ሃብት ቀውሶች አገሪቷን ወዳልተገባ አቅጣጫ እንዳመራት ይነገራል።
ከሰሞኑ ወታደራዊ ሃይሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክን በቁም እስር አቆይቶ በትናንትናው ዕለት የተፈቱ ሲሆን፤ አገሪቷ ያለችበትን ችግርም ፍንትው አድርጎ አሳይቷል።
የወታደር ሃይሉ ድርጊት ሱዳንን ወደተባባሰ ቀውስ ውስጥ እንዳያስገባት የሚለው የብዙዎች ስጋት ሆኗል።
የሱዳን የሽግግር ሉዓላዊ ምክር ቤት ሊቀ-መንበር ሌተናንት ጀነራል አብዱል ፋታህ አልቡርሀንም ጠቅላይ ሚኒስትር ሃምዶክን በቤታቸው ማስጠለላቸውን ገልጸው፤ይህም ለበጎ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህ የሆነው ባለፈው ሣምንት በሱዳን የተቀሰቀሰውን የፖለቲካ አለመረጋጋት ተከትሎ በአገሪቷ ሊመጣ የሚችለውን የፖለቲካ ቀውስ ለማስቀረት መሆኑን ነው የገለጹት።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአፍሪካ የእስያ ጥናት ማዕከል ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተፈራ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በአሁኑ ወቅት ሱዳን የገባችበት የፖለቲካ ቀውስ ለኢትዮጵያ ብሎም ለአካባቢው አገራት ስጋት የሚፈጥር ነው።
በመሆኑም በሱዳን ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር "ኢትዮጵያ የበኩሏን አዎንታዊ አስተዋጽዖ ማድረግ ይጠበቅባታል" ብለዋል።
ኢትዮጵያ በሱዳን ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ከሱዳን ሕዝብና ቅቡልነት ካለው ሕጋዊ መንግሥት ጎን በመቆም አዎንታዊ ሚናዋን መጫወት እንዳለባት ነው የገለጹት።
ኢትዮጵያ ከሱዳን ሕዝብ ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ግንኙነትና በተለይም "በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ያለውን ለዘመናት የቆየ ወዳጅነት የማስጠበቅ ሃላፊነቷን ልትወጣ ይጠበቅባታል" ብለዋል።
በምስራቅ አፍሪካ ሊኖር የታሰበው ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ብልጽግና ለማረጋገጥ ሰላም ስለሚያስፈልግ ኢትዮጵያ እንደ ኢጋድ አባል አገርነቷ ይህንን ሚና ልትጫወት እንደሚገባ ነው አጽንኦት የሰጡት።
በሱዳን አሁን ያለውን የፖለቲካ አለመረጋጋት ችግር መፍታት ካልተቻለ ለኢትዮጵያ አሉታዊ ጎኑ ስለሚሰፋ መንግሥት ጉዳዩን በአንክሮ ሊከታተለውና ሊያጤነው እንደሚገባም አሳስበዋል።
ኢትዮጵያ የሱዳንን ሰላም እውን እንዲሆን በአብዬ ግዛትና በዳርፉር እንዲሁም በጥምር መንግሥት ምሥረታ ላይ ያሏትን አስተዋጽዖዎች አጠናክራ ልትቀጥል እንደሚገባ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ያለው አጋርነት ጠንካራ መሆኑን ገልጸው፤ ሁለቱም አገራት ለሕዝባቸውና አካባቢው አገሮች የሚበጁ የጋራ ጉዳዮችን መሥራት እንዳለባቸው ነው ያስረዱት።
በዚህም አግባብ የሱዳን መንግሥት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና በተለይም በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ያለውን አለመግባባት በተመለከተ በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ዝንባሌዎችን ማዳበር እንደሚገባ ምከረ ሃሳብ ሰጥተዋል።
ሁለቱ አገራት ያላቸውን ሁለንተናዊ ግንኙነት በማጠናከር የጋራ በሚሏቸው ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ በመሥራት ለአካባቢው ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ልማት መትጋት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልእክት እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከቀናት በፊት ያወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ከሱዳን ህዝብ ጋር መቆሟን በይፋ ታረጋግጣለች ማለታቸው ይታወሳል።