ህብረተሰቡ ወራሪውን ኃይል ለማጥፋት እየተፋለመ ለሚገኘው ሠራዊት ደጀንነቱን መቀጠል አለበት - ኢዜአ አማርኛ
ህብረተሰቡ ወራሪውን ኃይል ለማጥፋት እየተፋለመ ለሚገኘው ሠራዊት ደጀንነቱን መቀጠል አለበት
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17/2014 /ኢዜአ/ ህብረተሰቡ ወራሪውን ኃይል ለማጥፋት እየተፋለመ ለሚገኘው ሠራዊት ደጀንነቱን መቀጠል አለበት ሲሉ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ /አብን/ ምክትል ሊቀ መንበር አቶ የሱፍ ኢብራሂም ተናገሩ።
ለአሸባሪው ህወሃት ሀሰት ወሬዎች ጆሮ ባለመስጠት ሰርጎ ገብ የወራሪ ኃይሉ የጥፋት መልዕክተኞች ላይ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እንዲያደርግም አስገንዝበዋል።
ወራሪውን የህወሓት ሽብርተኛ ኃይል ለማጥፋት በወሎ ግንባር እየተፋለመ የሚገኘው የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራና የሌሎች ክልሎች ልዩ ኃይሎች፣ ሚኒሻና ፋኖ በታላቅ ወኔና ጀብዱ አኩሪ ታሪክ እየፃፉ እንደሚገኙም ገልጸዋል።
በመሆኑም "ህብረተሰቡም ወራሪውን ኃይል ለማጥፋት እየተፋለመ ለሚገኘው ሠራዊት ደጀንነቱን መቀጠል አለበት" ብለዋል።
"ደሴን ለመያዝ ተቃርበናል" የሚሉ የአሸባሪው ህወሃት የሀሰት ወሬ አቀባባዮች ቀረርቶም የሽብር ቡድኑ የተለመደ የሃሰት ሙሾና ቅጥፈት እንደሆነ አመልክተዋል።
አሸባሪው ህወሃት የመከላከያ ሠራዊቱን ስም ለማጥፋት እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ ከመከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የመከላከያ ሰራዊቱን ስም ለማጥፋት ቢሞክርም እንደ እስካሁኑ ለእውነት እና ርትዕ በመቆም የድል ግስጋሴውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተገልጿል።