ቀጥታ፡

ማህበሩ በአሸባሪው ቡድን ወረራ ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ16 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ምግብና ቁሳቁስ ለገሰ

ባህር ዳር ፤ ጥቅምት 16/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በአሸባሪው የህወሃት ቡድን ወረራ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው እብናት መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ወገኖች ዛሬ ከ16 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ምግብና ቁሳቁስ ለገሰ።

በማህበሩ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሻንበል ዋለ እንደገለፁት፤ ማህበሩ በተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ወገኖችን በመደገፍ ማህበራዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል።

ዛሬ በማህበሩ የተለገሰው አሸባሪው ቡድን ወረራ  ከዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው እብናት የመጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ 3ሺህ አባወራዎች ነው።

የምግብ ዱቄት፣ ዘይት ፣ የሴቶች ንፅህና መጠበቂያ፣ አልባሳት ፣ድንኳኖችና የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች ከተለገሰው ውስጥ እንደሚገኙበት አስረድተዋል።

በቀጣይም  የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ ቀያቸው ተመልሰው እስኪቋቋሙ ማህበሩ የሚያደርገውን የሰብአዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ሃላፊው አስታውቀዋል።

ቀደም ሲል ማህበሩ ከዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ጋር  በመተባበር  በዳባት ፣ደሴ፣ ባህር ዳር እና እብናት ለሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖች ከ134 ሚሊየን 500ሺህ ብር በላይ ግምት ያለው ምግብና የምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁስ  ድጋፍ ማድረጉም አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም