ቀጥታ፡

ተግዳሮቶች እየሰፉ በመጡበት በዚህ ወቅት ከሱዳን ሕዝቦች ጎን በሙሉ ልባችን እንቆማለን

ጥቅምት 16 ቀን 2014 (ኢዜአ) “ተግዳሮቶች እየሰፉ በመጡበት በዚህ ወቅት ከሱዳን ሕዝቦች ጎን በሙሉ ልባችን የምንቆም መሆናችንን በድጋሚ እናረጋግጣለን” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ወቅታዊዉን የሱዳን ሁኔታ በተመለከተ በይፋዊ የፌስቡክ ገጻቸው በአረብኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸው የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕዝብ በወንድም ሱዳን ሀገር እየተካሄደ ያለውን ሁኔታ በቅርበት እየተከታተሉ እንደሆነ ገልጸዋል።

ይህም ለበርካታ ዘመናት ከተሻገረው የሁለቱ ሕዝቦቻችን ትስስር የመነጨ እንደሆነ አመልክተዋል።

“ከዚህም ባሻገር ይህ ሁለቱ ሕዝቦቻችን ከሚጋሩት የጋራ መጻኢ ዕጣ ፈንታ እና የጋራቸው ከሆነ የናይል ስልጣኔ፣ ታሪክ እና የመቻቻል እሴት የመነጨ ነው” ብለዋል።

የወንድም ሕዝቦች ሀገር ሱዳን በታሪኳ ባሳለፈችው አስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ኅብረት ጋር በመሆን በወታደራዊው እና በሲቪሉ መካከል የሀሳብ መቀራረብን ለማምጣት መስራቷን አስታውሰዋል።

“የሕገመንግሥታዊ ሰነዱ መሠረት የሆነ ሚናን በመጫወት ታሪካዊ ኃላፊነቷን መወጣቷን ማስታወስ እጅግ ዋጋ ይኖረዋል” ሲሉም ገልጸዋል።

“ከዚህ ወቅታዊ ሁኔታ ውስጥ መውጫ መንገድ እንዳለ ያለንን እምነት እና ተስፋ በምንገልጽበት በዚህ ወቅት፤ የፖለቲካ ልዩነቶች መስፋት እና የችግሮች መባባስ ስጋት እንዳለብንም መግለጽ እንሻለን” ብለዋል።

የሕገ መንግስታዊ ሰነዱ ቃል ኪዳን እሴቶች ለማስጠበቅ እና የጁባ ሰላም ስምምነት ነጥቦችን በማስከበር የሱዳን ሕዝቦችን ብሩህ የሆነ መጻኢ ጊዜ ተስፋን ዕውን ለማድረግ የሱዳን ሀገር በቀል ጥበብና ልምዶች በቂ አቅም እንደሆኑ ጽኑ እምነት እንዳላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

“በመሆኑም በዚህ የአፍሪካ ቀንድ ቀጠና በአጠቃላይ በፈታኝ ሁኔታ ውስጥ እያለፈ በሚገኝበት እና ተግዳሮቶች እየሰፉ በመጡበት በዚህ ወቅት ከሱዳን ሕዝቦች ጎን በሙሉ ልባችን የምንቆም መሆናችንን በድጋሚ እናረጋግጣለን” ብለዋል።

“ከዚህም ባሻገር በቀጠናችን የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ በመግባት ለሉዓላዊና ነጻ ውሳኔዎቻችን ያነሰ ግምት በመስጠት ፍላጎታቸውን ለመጫን የሚጥሩ ኃይሎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ እናስጠነቅቃለን” ሲሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም