የመከላከያ ሰራዊት አባልነት ኢትዮጵያዊነትን በጥልቅ የሚታወቅበት፣ ለአገር የማገልገል ክብር የሚታይበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመከላከያ ሰራዊት አባልነት ኢትዮጵያዊነትን በጥልቅ የሚታወቅበት፣ ለአገር የማገልገል ክብር የሚታይበት ነው
ጥቅምት 16/2014 (ኢዜአ) የመከላከያ ሰራዊት አባል "ስትሆን ኢትዮጵያዊነትን በጥልቅ የሚታወቅበት፣ ለአገር የማገልገል ክብርን የታይበት ነው" ሲሉ በሰላም ማስከበር ማዕከል የሁርሶ ኮንቲንጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ምልምል ወታደሮች ተናገሩ።
የጠላት ዐይን ቀልብ ማረፊያ የሆነችው ምድረ ቀደምቷ ኢትዮጵያ ለዕልፍ ዘመናት በጠላት ብትፈተንም በዜጎቿ መስዕዋትነት ድል ነስታ፤ ሕልውናዋን አስጠብቃ ዛሬ ደርሳለች።
እናም በየታሪኳ ምዕራፏ ጦርነት ያልተለያት ኢትዮጵያ በጠላት ስትወረር ኢትዮጵያዊያን ያለማመንታት በክተት ጥሪ ዘመቻ የመትመም፤ ፀረ ኢትዮጵያ ሃይላትን የማሳፈር ነባር እሴታቸው ዛሬም ቀጥሏል።
አሁን ላይ የታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች በትሮይፈረስነት የሚንቀሳቀሱ ውስጣዊ ባንዳዎች ወረራ ሲፈጽሙ፤ በርካታ ዜጎች ቅድሚያ ለኢትዮጵያ ህልውና በሚል የመከላከያ ሰራዊትን ተቀላቅለዋል።
ለዚህ አብነትም ከአዊ ዞን በመምህርነት ሙያ የተሰራማው እንዳለው አለለት፤ በወልቂጤ ከተማ በሚገኝ ሆስፒታል በነርስነት የሚሰራው ወጣት ፀጋዬ ተስፋሁ እና በሹፌርነት ሙያ የተሰማራው የባህር ዳር ነዋሪ አበራ ጌታነህ ማሳያ ናቸው።
ወጣቶቹ አገር ለማፍረስ ጥቃት በከፈተው አሸባሪው ቡድን ድርጊት በመበሳጨታቸው ኢትዮጵያ በአሸባሪው ቡድን እየደረሰባት ያለውን ጥቃት ለመከላከል ስራቸውን አቁመው ወደ ሁርሶ ኮንቲንጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ከትመዋል።
"አገር እናት ናት፤ እናት ስትደፈር ደግሞ ቁሞ መመልከት አላስቻለንም" የሚሉት ምልምል ሰልጣኞቹ፤ "አገር ህልውናዋ ከተጠበቀ ሌላው ስራ ሁሉ ይደረስበታል" የሚል እምነት አላቸው።
በተመሳሳይ የተሰማራበትን ስራ አቁሞ ውትድርናን የተቀላቀለው የአርባምንጭ ነዋሪው ሶዶ ማረ፣ የባህር ዳር ነዋሪው ኤልያስ መኩሪያው እና የ2013 የመካኒካል ምህንድስና ምሩቁ የጅማው ወጣት በረከት ስንታየሁም ቅድሚያ ለአገር ብለው ለእናት አገር ጥሪ ከተዋል።
"በእኛ ትውልድ አገር አትፈርስም" የሚሉት ሰልጣኞቹ፤ በትምህርት ቤቱ በቂ ስልጠናዎች እያገኙ ስለመሆኑና አገራቸውን በወታደርነት ለማገልገል ሰራዊቱን በመቀላቀላቸው እድለኞች እንደሆኑ ገልጸዋል።
መከላከያ ሰራዊት አገርን ሕልውና ከማስከበር ባሻገር በተለይም ለተማሩ ወጣቶች ትልቅ የሙያ ዕድሎች የሚገኝበት ተቋም እንደሆነ ይናገራሉ።
መከላከያ ሰራዊት ኢትዮጵያዊነት የሚታወቅበት፣ ለአገር የማገልገል ክብር የሚታይበት ተቋም እንደሆነ ገልጸው፤ ለሌሎች ወጣቶች በሕልውና ዘመቻው ጥሪ መሰረት አገርን ለማገልገል እንዲቀላቀሉ ጠይቀዋል።