ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በጋራ ለመስራት ተፈራርሙ

ጥቅምት 16/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ዳይሬክተር ዶክተር ኢንጅነር አብዮት ሲናሞ እንዳሉት፤ስምምነቱ ባለስልጣኑ የኤሌክትሮኒክስ የታገዘ ፈጣን አገልግሎት እንዲሰጥ ያስችለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት በመስጠት ረገድ ለውጥ ለማምጣት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በ10 ዓመቱ መሪ እቅድ 80 በመቶ የሚሆኑ የመንግስት ተቋማትን የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ እቅድ መያዙን ለአብነት አንስተዋል፡፡

በአገሪቱ እስካሁን ባለው ሂደት 41 ተቋማት የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት መስጫ ሶፍትዌሮችን በማልማት ወደ ስራ መግባታቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ካለፈው ዓመት ጀምሮ አሰራሩን ለማዘመን የተለያዩ ስራዎች እያከናወነ ይገኛል።

ከዚህ አኳያ ስምምነቱ የደንበኞችን መጉላላት በመቀነስ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ከፍትኛ እገዛ አለው ብለዋል።

በስምምነቱ መሰረት ተገልጋዮች ባሉበት ቦታ ሆነው ባለስልጣኑ የሚሰጣቸውን 13 የሚሆኑ የአገልግሎቶችን በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ አመካኝነት በመጠቀም ይችላሉ ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም