የአሸባሪውን ህወሃት መቃብር በወሎ ለማድረግ በሚደረገው ዘመቻ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ተሳትፎውን ማስቀጠል አለበት - ኢዜአ አማርኛ
የአሸባሪውን ህወሃት መቃብር በወሎ ለማድረግ በሚደረገው ዘመቻ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ተሳትፎውን ማስቀጠል አለበት
ጥቅምት 16 /2014 (ኢዜአ) አሸባሪውን የህወሃት ወራሪ ኃይል መቃብር በወሎ ለማድረግ በሚደረገው የህልውና ዘመቻ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እያደረገ ያለውን ተሳትፎ እንዲያስቀጥል የደቡብ ወሎ ዞን ጥሪ አቀረበ።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱ ሁሴን በዞኑ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ አሸባሪው ህወሃት የአማራን ህዝብ በጠላትነት ፈርጆ የአርሶ አደሩን ሃብት ንብረት እና ልጆቹን በማጥፋት ግዛት ለማስፋፋት እየጣረ መሆኑን አመላክተዋል።
ወራሪው ኃይል እንደ ትምህርት ቤትና ጤና ጣቢያ ያሉ ማህበራዊ አገልግሎት ሰጪ መሰረተ ልማቶችን ማውደሙን ገልጸዋል።
ምጣኔ ሃብታዊ መሰረተ ልማቶችም የአሸባሪው ቡድን የጥቃት ኢላማ መሆናቸውን ተናግረዋል።ቡድኑን ለማጥፋት የአገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይልና ሌሎች የጸጥታ አደረጃጀቶች በጀግንነት እየተፋለሙት እንደሚገኙ አመላክተዋል።
በዞኑ ያለው ማህበረሰብም የጥፋት ቡድኑን እኩይ አላማ በሚገባ በመረዳት ግንባር ላይ ተጋድሎ እያደረገ ለሚገኘው ሰራዊት ድጋፍ በማድረግ ደጀንነቱን እያሳየ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ወጣቶች በየኬላው ድንገተኛ ፍተሻ በማድረግ የሽብር ቡድኑን ሰርጎ ገብ ተላላኪ በቁጥጥር ስር በማዋል ከጸጥታ ኃይሉ ጋር እየሰሩ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ከተለያዩ የክልሉ ክፍሎች የተውጣጡ ባለሃብቶች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች፣ ፋኖዎችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ለህልውና ዘመቻው ከፍተኛ ድጋፍ በማድረግ ለሰራዊቱ ደጀንነታቸውን እያስቀጠሉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በቀጣይም ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሽብርተኛው ወራሪ ኃይል መቃብር በወሎ ለማድረግ ለሚደረገው ተጋድሎ የሚያደርጉትን ተሳትፎ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።