ቀጥታ፡

ኢትዮጵያን ለማፍረስ በተነሳው የሕወሓት የሽብር ቡድን ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት

ጥቅምት 16/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያን ለማፍረስ በተነሳው የህወሃት አሸባሪ ቡድን ላይ የሚወሰደው እርምጃ ሊጠናከር እንደሚገባ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተናገሩ።

የሕወሃት የሽብር ቡድን የሚጠቀምባቸውን የጦር መሳሪያ ማምረቻ፣ ወታደራዊ ማሰልጠኛና ወታደራዊ ልብስ አስመስሎ የሚያመርትባቸው የተመረጡ ስፍራዎች ሰሞኑን በአየር ሃይል ከጥቅም ውጭ እንዲሆኑ ተደርጓል።

ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም ቢሆን እገባለሁ ብሎ የተነሳው የህወሃት የሽብር ቡድን ሰርጎ በሚገባባቸው አካባቢዎች በንፁሃን ላይ ግዲያ ከመፈፀም በተጨማሪ የግልና ህዝባዊ ተቋማትን እያወደመ ይገኛል።

በመሆኑም ይህንን አሸባሪ ቡድን ለማጥፋት በመንግስት የሚወሰደው እርምጃ ሊጠናከር እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው የተፊካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ /ኢህአፓ/ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አብርሃም ኃይማኖት፤ ሕወሃት አገር ለማጥፋት የሚጠቀምባቸውን የተመረጡ ስፍራዎች በመለየት በአየር ሃይላችን እንዲወድሙ መደረጉን ፓርቲያችን ይደግፋል ብለዋል።

በቀጣይም የሽበር ቡድኑ የሚጠቀምባቸውን የተመረጡ ቦታዎች ማውደም ይገባል ነው ያሉት።

የኦሮሞ ነጻነት ንቅናቄ ሊቀመንበር አቶ ደረጀ በቀለ በበኩላቸው አሸባሪው ቡድን በአማራና አፋር ክልሎች የሚፈጽመውን ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች ቀጥሎበታል ብለዋል።

የሽብር ቡድኑን እኩይ አላማ ለማክሸፍ መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ በማጠናከር ጦርነቱን በአጭር ጊዜ አጠናቆ ሙሉ ለሙሉ ፊቱን ወደ ልማት ማዞር አለበት ሲሉ ተናግረዋል።

በተለይም የውጭ ኃይሎች በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባትና የኢትዮጵያን ሉአላዊነት አደጋ ላይ ለመጣል የሚያደርጉትን ጥረት መንግሥት ባለመቀበል ግልጽ አቋም መያዙን አቶ ደረጀ  አድንቀዋል።

አሜሪካ እና አንዳንድ የምእራቡ ዓለም አገራት በምርጫ ሥልጣን የያዘ መንግሥት እያለ በሽብርተኝነት ከተፈረጀ ቡድን ጎን መቆማቸው ፍፁም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ተናግረዋል።

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሃይል ንቅናቄ የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ አቶ የራስወርቅ መላኩ በበኩላቸው የህወሃት የሽብር ቡድን ኢትዮጵያ እንደ አገር እንዳትቀጥል ላለፉት 30 ዓመታት ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል።

አሁንም ኢትዮጵያ እንደ አገር እንዳትቀጥል ሽብር በመፈፀም ያለ የሌለ ሃይሉን እየተጠቀመ መሆኑን ገልጸዋል።

"የሽብር ቡድኑን ለማጥፋት ሁላችንም በጋራ የምንቆምበት ጊዜ አሁን ነው" ያሉት የህዳሴ ፓርቲ ዋና ጸሃፊ ኢንጅነር ሱራፌል እሸቱ ናቸው።

የፓርቲዎቹ አመራሮች የአገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር በሚደረገው ዘመቻ በተግባር አጋርነታቸውን እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም