ቀጥታ፡

የአባቶቻችንን የጀግንነት ታሪክ እናስቀጥላለን

ደሴ ፤ ጥቅምት 16/2014(ኢዜአ)አሸባሪው ህወሓት የከፈተውን ጦርነት በመቀልበስ የአባቶችን የጀግንነት ታሪክ እንደሚያስቀጥሉ የደሴ ከተማ ወጣቶች አስታወቁ።

የወጣቶቹ አስተባባሪ ይልማ ተረፈ ፤  የከተማዋ ወጣቶች የጥፋት ተግባር ለመፈጸም እየተንቀሳቀሰ ያለውን አሸባሪ ቡድን ግብዓተ መሬት በመፈጸም  ታሪክ ለማስመዝገብ መዘጋጀታቸውን  ገልጸዋል።

ወራሪው ቡድን  ወደ ደሴና አካባቢዋ ሰርጎ እንዳይገባ ወጣቶች ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር ተቀናጅተው ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል እያደረጉ መሆናቸውን ተናግሯል።

በከተማዋ ዛሬ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ድንገተኛ ፍተሻ እየተደረገ መሆኑን በማመልከት፡፡

በአሸባሪው ቡድን ቀብር ላይ ለመሳተፍ ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ ወጣቶች ወደ ወሎ ግንባር እየተመሙ መሆናቸውንም አስታውቋል።

በከተማዋ የአራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወጣት ይመር ሰይድ ፤ ወሎን የአሸባሪው የህወሃት ወራሪ ኃይል መቃብር ለማድረግ ከመከላከያ ሠራዊት፤ከአማራ ልዩ ሃይልና ከሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ጎን መሰለፉን ገልጿል፡፡

''የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ነጻነት በደምና በአጥንታችን እናስቀጥላለን'' ብሏል ወጣት ይመር።

የህይወት መስዋዕትነት ጭምር ከፍለን አካባቢያችንን በመጠበቅ የሽብር ቡድኑን በመቅበር ታሪክ እንሰራለን ያለው ደግሞ  የመናፈሻ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወጣት ቢኒያም የሱፍ ነው።

የሀገር ሉዓላዊነት ለማስከበር ከሚዋደቁት የጸጥታ ኃይሎች ጎን በመሆን ወራሪው ዳግም እንዳይነሳ በማድረግ ሕዝብና ሀገሪቱን  ነጻ እንደሚያወጡ ተናግሯል፡፡

ተቀናጅተው  ቡድኑን በመቅበር የአባቶችን የጀግንነት ታሪክ እንደሚያስቀጥሉ ነው ወጣቶቹ ያስታወቁት።

የደሴ ከተማ ዛሬም የተለመደ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዋን እያከናወነች መሆኗን ከሥፍራው ተዘግቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም