የኢትዮጵያ መንግስት እያካሄደ ያለውን የልማትና የለውጥ ሥራዎች ለመደገፍ የአውሮፓ ህብረት ፍላጎት አለው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መንግስት እያካሄደ ያለውን የልማትና የለውጥ ሥራዎች ለመደገፍ የአውሮፓ ህብረት ፍላጎት አለው
ጥቅምት 16/2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያ መንግስት እያካሄደ ያለውን የልማትና የለውጥ ሥራዎች ለመደገፍ የአውሮፓ ህብረት ፍላጎት አለው ሲሉ የህብረቱ የአለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ጁታ ዩራፕሌኒን ገልጸዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የአውሮፓ ህብረት የአለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ጁታ ዩራፕሌኒን እና የህብረቱ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካይ ዶ/ር አኔቲ ዌበርን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡
ኮሚሽነሯ በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ ስኬታማ ምርጫ በመካሄዱ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፤ አዲሱ መንግስት በአገሪቱ ያለው የፀጥታ ችግሮችን እና አስተዳደራዊ ጉዳዮች በተመለከተ እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎች ዙሪያ ማብራሪያ ጠይቀዋል፡፡
ኮሚሽነሯ በአውሮፓ ህብረት እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ግንኙነት በማስታወስ፤ ህብረቱ አሁንም በኢነርጂ፣ በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ ፣በጤና፣ በኮቪድ-19፣ በሰብአዊ ልማት፣ የግል ሴክተርን በማበረታታትእና መልካም አስተዳደር ዙሪያ ድጋፎቹን አጠናክሮ ለመቀጠል ዕቅድ እንዳለው አመላክተዋል፡፡
አክለውም መንግስት እያካሄደ ያለውን የልማትና የለውጥ ሥራዎች ለመደገፍ ህብረቱ ፍላጎት እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ሁሉንም የፖለቲካ ሃይሎችን ያቀፈ ውይይት እንዲጀመር፣ የሰብአዊ ዕርዳታ ተደራሽ እንዲሆን፣ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በገለልተኛ አካላት እንዲጣሩ እና አጥፊዎች በህግ እንዲጠየቁ ኮሚሸነር ጁታ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው የሰብአዊ ዕርዳታ ተደራሽ እንዲሆን መንግስት በቁርጠኝነት በርካታ እርምጃዎች መውሰዱን አብራርተዋል፡፡
የሰብአዊ መብት ጥሰት ምርመራም በጠቅላይ አቃቤ ህግ እንዲሁም ከአለም አቀፍ ተቋም ጋር በጥምር መደረጉን ጠቅሰው፤ የሰብአዊ መብት ጥሰት ፈጻሚዎችን ተጠያቂ ለማድረግ በመንግስት በኩል የማያወላዳ አቋም መኖሩን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥስት አሸባሪው ሕወሃት የደቀነውን አደጋ ከመከላከል ጎን ለጎን የሚያካሂደውን የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ የአውሮፓ ህብረት ሊደግፍ እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አስታውቀዋል።
በአገሪቱ አዲስ የፖለቲካ ባህል ሶስት የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችን በማካተት አዲስ መንግስት መመሥረቱን ገልጸዋል፡፡
ሁሉን አቀፍ ውይይቶችን ለማካሄድ ቅድመ-ዝግጅቶች እየተደረገ መሆኑን አብራርተው የአፍሪካን ህብረት በመወከል ለሚያደራድሩት ለቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ለኦሉሴንጎን ኦባሳንጆ ህብረቱ ስለሰጠው ድጋፍ አቶ ደመቀ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በአማራ እና አፋር ክልሎች የሰብአዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች፤ ህብረቱ በአየር የሰብአዊ ዕርዳታ እንዲያደርስ ጠይቀው፤ የህወሃት ቡድን በአማራ እና አፋር ክልል ከያዛቸው ቦታዎች ለቆ እንዲወጣ ህብረቱ ግፊት እንዲያደርግ እንዲሁም ድርጊቱን ማውገዝ እንደሚጠበቅበት አቶ ደመቀ ተናግረዋል።
በህብረቱና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ግንኙነት በማሻሻል፤ ቀጣይ የፖለቲካ ምክክሮችን በማድረግ ልዩነቶችን በማጥበብ እና የነበረውን ግንኙነት አጠናክሮ ለማስቀጠል አመቺ ጊዜ መሆኑን ነው አቶ ደመቀ ያመላከቱት።