ቀጥታ፡

በሰሜን አሜሪካ ለሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ጳጳሳት በወቅታዊ ሁኔታ ላይ ማብራሪያ ተሰጠ

ጥቅምት 16 ቀን 2014 (ኢዜአ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በሰሜን አሜሪካ ለሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ጳጳሳት በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ማብራሪያ ሰጡ።

ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታና ይህን የችግር ጊዜ ቤተክርስቲያኒቱ ከመንግስት ጋር በመተባበር ስለመፍታት ለመምከር በኢትዮጵያ የሚገኙትን ጳጳሳት አቶ ደመቀ መኮንን ትናንት በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

በውይይቱም ጳጳሳቱ የአገራቸውን እውነት በሰሜን አሜሪካ ላሉ የመንግስት ተቋማት ለማሳወቅ የሚያስችላቸውን መረጃ እንዲያገኙ ተደርጓል።

አቶ ደመቀ በሰጡት ማብራሪያ አሸባሪው ህወሃት በኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅምና እና በኢትዮጵያ ህዝቦች ላይ እያሳደረ ስላለው ጫና አስረድተው፤ በየትኛውም ዘርፍ ያሉ ኢትዮጵያውያን አንድነትና ትብብር በመፍጠር ጠላትን እንዲዋጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የቤተክርስቲያኒቱ መሪ አባቶቹ ከአትላንታ፣ ጆርጅያ፣ ኒውዮርክ፣ ኮሎራዶ፣ ደቡብ ካሊፎርኒያ፣ ዋሽንግተን ዲሲ፣ ሲያትል፣ ሜኒሶታ እና ካናዳ የመጡ ናቸው፡፡

በሰሜን አሜሪካ ያሉ የኢትዮጵያ ጳጳሳት የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታን በማስመልከት ተደጋጋሚ ውይይት ከአሜሪካን መንግስት፣ ከአሜሪካ የሴኔት አባላትና ከአሜሪካ የህዝብ ተወካዮች አባላት ጋር ማድረጋቸውን ከውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም