ኢትዮጵያዊነትን፣ አንድነትና ፍቅርን ሰባኪ ከያኒያን ሰንደቅ ዓላማን ከፍ አድርገው በሙያቸው መስዋዕትነት ሲከፍሉ ቆይተዋል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያዊነትን፣ አንድነትና ፍቅርን ሰባኪ ከያኒያን ሰንደቅ ዓላማን ከፍ አድርገው በሙያቸው መስዋዕትነት ሲከፍሉ ቆይተዋል
ጥቅምት 15 ቀን 2014 (ኢዜአ) “ኢትዮጵያዊነትን፣ አንድነትና ፍቅርን ሰባኪ ከያኒያን ሁሌም ሰንደቅ ዓላማን ከፍ አድርገው በሙያቸው መስዋዕትነት ሲከፍሉ ቆይተዋል” ሲሉ የሁርሶ ኮንቲንጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ዋና አዛዥ ኮሎኔል አዲሱ ተርፋሳ ገለጹ።
ታዋቂ አንጋፋና ወጣት ድምጻዊያን ከዛየን ባንድ ጋር ተቀናጅተው "ቅድሚያ ለእናት ሀገር" በሚል መሪ ሀሳብ በሁርሶ ኮንቲንጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ለአራተኛ ዙር ምልምል ሰልጣኞች ስራቸውን አቅርበዋል።
በሰላም ማስከበር ማዕከል የሁርሶ ኮንቲንጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ዋና አዛዥ ኮሎኔል አዲሱ ተርፋሳ እንደገለጹት፤ ከያኒያን በሙያቸው ለሀገር መስዋዕትነት ሲከፍሉ ቆይተዋል።
ዛሬም ሀገር በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆና አለኝታ መሆናቸውን ገልጸው፤ ለምልምል ወታደሮች የሞራል ስንቅ ለማቀበል በማሰልጠኛ ትምህርት ቤቱ በመገኘታቸው አመስግነዋል።
"ውትድርና እና ኪነ-ጥበብ የተሳሰሩት በኢትዮጵያዊነት ብቻ ሳይሆን በሙያም ጭምር ነው" ያሉት ዋና አዛዡ፤ ወታደር ለድል የሚበቃው በመተኮስ ብቻ ሳይሆን በኪነ ጥበብ አነሳሽነትና ሞራል ሲሰንቅ መሆኑን ገልጸዋል።
ኪነ-ጥበብና ወታደርነት ችግርን በብርታት መሻገር፣ ለአገር አንድነትና ፍቅር ዋጋ መክፈል እንደሚያመሳስላቸው ጠቁመው፤ "የኢትዮጵያ ወታደር ለአገሩ የሚሰዋ፣ በስነ ምግባር የታነጸ ሃይል ነው" ብለዋል።
"ኢትዮጵያዊ መሆን በራሱ ጀግንነትና ኩራት ነው” ያሉት ዋና አዛዡ፤ የኢትዮጵያ ወታደር አብሮ መብላትን፣ ደግነትን፣ ለዓላማ መስዕዋት መሆንንና የሀገር ክብርን ማስቀደም የተማረ ነው" ብለዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው ምልምል ሰልጣኞችም የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በስልጠና ትምህርት ቤቱ ተገኝተው ስራቸውን በማቅረባቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል፤ አመስግነዋልም።
ከድምጻዊያን መካከልም አረጋኸኝ ወራሽ፣ ጸጋዬ እሸቱ፣ ግርማ ተፈራ፣ ታደለ ሮባ፣ ማዲንጐ አፈወርቅ፣ ጌታቸው ሃይለማርያም፣ ግርማ ተፈራ፣ መሰረት በለጠ፣ መስፍን በቀለ፣ ጌትሽ ማሞ፣ ማሚላ ሉቃስ፣ ጥላሁን አወቀና ሌሎች አርቲስቶች ይገኙበታል።