የዜጎች ሕይወት እንዲሻሻልና ቁጠባ ወሳኝ የሕይወት መርህ እንዲሆን እንሰራለን

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 15 ቀን 2014 (ኢዜአ) ዜጎች የተሻለ ሕይወት እንዲኖሩና ገቢያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ቁጠባ ወሳኝ የሕይወት መርህ እንዲሆን እንሰራለን ሲሉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለ3ኛ ጊዜ ያዘጋጀውና ለ45 ቀናት የሚቆየው "ለተሻለ ነገ ዛሬ ይቆጥቡ" የተሰኘው አገር አቀፍ የቁጠባ ንቅናቄ መርሃ ግብር ዛሬ ተጀምሯል።

መርሃ ግብሩን ያስጀመሩት የባንኩ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ የምርት ምጣኔና ቁጠባ ለአገራዊ እድገት ያላቸው አስተዋጽኦ ሚዛኑን እንዲጠብቅ መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። 

አገራዊ ልማት እንዲሳካ፣ ዜጎች የተሻለ ሕይወት እንዲኖሩና ገቢያቸውን በጥንቃቄ እንዲጠቀሙ ቁጠባ ወሳኝ የሕይወት መርህ እንዲሆን እንሰራለን ብለዋል።

የተረጋጋ ሕይወት መምራትና ሃብት ማፍራት እንዲቻል የቁጠባን ባህል ማዳበር እንደሚገባም ነው ያመለከቱት።

ለዚህም ተከታታይና ሰፊ የሕዝብ ንቅናቄ ለመፍጠር 3ኛው አገር አቀፍ የቁጠባ መርሃ ግብር መጀመሩን ገልጸዋል።  

የቁጠባን ግንዛቤ ለማሳደግ፣ ትክክለኛ የገንዘብ ማስቀመጫ ባንክ መሆኑን ለማስገንዘብና ተጨማሪ አዳዲስ ቆጣቢ ዜጎችን ለማፍራት እየተሰራ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

የዜጎችን የቁጠባ ባህል ለማሳደግ ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን የጠቀሱት አቶ አቤ ቁጠባ ስላለው ጠቀሜታ በአገር፣ በቤተሰብ፣ በተማሪዎችና ህጻናት ጭምር የግንዛቤ ስራዎች ይቀጥላሉ ብለዋል።

በንቅናቄው ተማሪዎች፣ አርሶ አደሮች፣ የመከላከያ ሠራዊትና  የፖሊስ አባላት፣ በንግድ ስራ የተሰማሩ፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች  እንደሚሳተፉም ገልጸዋል።

ቁጠባን ባህል ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።

በ1938 ዓ.ም የመጀመሪያውን የቁጠባ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ባንኩ በርካታ የቁጠባ አማራጮችን ቢተገብርም የገጠር ወረዳዎችና ከከተማ የራቁ ዜጎችን የፋይናንስ አካታችነትና የባንክ አገልግሎት በተሟላ መልኩ ለማሳካት አሁንም በርካታ ስራዎች እንደሚፈልግ ጠቁመዋል።

እ.አ.አ 2018 የኢትዮጵያ አገራዊ ቁጠባ ወይም ወደ ባንኮች የገባ የቁጠባ ገንዘብ 638 ቢሊዮን ብር ሲሆን በ2021 ወደ 1 ነጥብ 4 ትሪሊዮን ብር ማደጉን አቶ አቤ ሳኖ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም