ቀጥታ፡

የደጀንነት ድጋፋችንን አጠናክረን ቀጥለናል

ደሴ፤ ጥቅምት 15/2014(ኢዜአ) የፀጥታ ኃይሎች በአሸባሪው የህወሓት ቡድን ላይ እየወሰዱ ያለውን እርምጃ በመደገፍ ደጀንነታቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውን የደሴ ከተማ ነጋዴዎች አስታወቁ፡፡

ነጋዴዎቹ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤  የሀገር ህልውና ለማስጠበቅ ለዘመቱት ኃይሎች ድጋፍ እያደረጉ የንግድ እንቅስቃሴያቸውን እያከናወኑ ናቸው።

በከተማው በንግድ ሥራ የተሰማሩት አቶ ጀማል አወል ፤አሸባሪው የህወሓት ቡድን በለመደው የውሸት ወሬ ማፈናቀልና መዝረፍ እንደማይችል ይገልጻሉ።

ቡድኑ  ደሴን ተቆጣጥሬያለሁ  ካለ ሳምንት ቢያስቆጥርም እኛ በተረጋጋ ሁኔታ ሥራችንን እያከናወንን ወሎ መቀበሪያው እንዲሆን በቅንጅት እየሰራን ነው ብለዋል፡፡

ለጀግናው መከላከያ ሠራዊትና ለሌሎች የጸጥታ ኃይሎች በተሰባሰበው ገንዘብ ውሃ፣ ደረቅ ስንቅና ሌሎች ግብዓቶች በማቅረብ ደጀንነታቸውን በማሳየት ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

በሽብር ቡድኑ የውሸት ወሬ ተደናግጠው ሱቆቻቸው የዘጉት እንዲከፍቱ በማድረግ የከተማዋ የንግድ እንቅስቃሴ እንዳይቀዛቀዝ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን ተናግረዋል።

በሸቀጣ ሸቀጥ ሥራ የተሰማሩት ወይዘሮ ዘሐራ ዓሊ በበኩላቸው፤ ጊዜው ሽብርተኛውን ቡድን በመቅበር ታሪክ የምንሰራበት ነው ይላሉ።

ሥራቸውን እያከናወኑ ደጀንነትን ማጠናከር ደግሞ የህልውና ጉዳይ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

ከሰሞኑም 30ሺህ ብር ያህል ወጪ በማድረግ እሽግ ውሃ፣ ብስኩትና  ሌሎች ግብዓቶች ወደ ግንባር መላካቸውን ገልጸዋል፡፡

በውሸት ወሬ ከተማችንን ለቀን ሥራ የምናቆም ሳንሆን፤ ተደራጅተን የአሸባሪው ህወሓት ወራሪ ኃይል ወሎ ላይ ይደመሰሳል'' ያለው ደግሞ በጫማ ንግድ ሥራ የተሰማራው ወጣት ደመላሽ ጉግሳ ነው፡፡

''ከተማችንና ንብረታችንን ትተን የትም አንሄድም፤ የመጨረሻውን ድል እስከምናስመዝግብ ድረስም ሁለንተናዊ ተሳትፏችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብሏል፡፡

ከተለያዩ አካባቢዎች የሽብር ቡድኑን በወሎ ምድር ለመቅበር ወደ ወሎ የሚተሙ ወጣቶችና የተለያዩ አደረጃጀቶች ወኔና ብርታት እንደሰጣቸው ገልጿል፡፡

የኢዜአ ሪፖርተር በደሴ ከተማ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ተዘዋውሮ እንዳረጋገጠው የንግድና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት  ሥራቸውን በሰላም  እያከናወኑ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም