ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ መንግስት በሱዳን የሚገኙ ሁሉም ወገኖች በሰላማዊ ሁኔታ ችግሮችን እንዲፈቱ ጥሪ አቀረበ

ጥቅምት 15 ቀን 2014 (ኢዜአ) በሱዳን የተፈጠረውን ችግር ሁሉም ወገኖች በሰላማዊ ሁኔታ እንዲፈቱ የኢትዮጵያ መንግስት ፍላጎት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሱዳን የተከሰተውን መፈንቅለ መንግስትና ህዝባዊ ተቃውሞን በተመለከተ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ አውጥቷል።

በመግለጫው የኢትዮጵያ መንግሰት የሁለቱን ህዝቦች ለከፍለ ዘመናት የቆየ ወንድማማችነትን በሚያጠናክር መልኩ ሱዳን አሁን ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ በቅርበት እየተከታተለ እንደሚገኝ ገልጿል።

በሲቪል መንግስቱና በወታደራዊ ሃይሉ መካከል የስልጣን ሽግግር በሚካሄድበት ሁኔታ ላይ የኢትዮጵያ መንግሰት ኩሰዳን ጋር በቅርበት ሲሰራ መቆቱንም አስታውሷል።

አሁንም “በሱዳን የተፈጠረውን ችግር ለመቅረፍ ሁሉም ወገኖች በሰላማዊ ሁኔታ እንዲሰሩ የኢትዮጵያ መንግስት ጥሪውን ያቀርባል” ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

በዚህ ሂደት የሱዳን መንግስት በሚያካሂደው የዴሞክራሲ ግንባታና የሽግግር ህገ መንግስቱ ላይ በሰፈረው መርህ መሰረት ኢትዮጵያ ድጋፏን እንደምታደርግ ገልጿል።

“ኢትዮጵያ የሱዳን ሉዐላዊነት የማይጣስበትና የሱዳናውያን ፍላጎት የሚከበርበትን መርህ እንዲጠበቅና የውጭ ሃይሎች በአገሪቱ ጣልቃ አለመግባታቸው አስፈላጊነትን በድጋሚ ታስገነዝባለች” ብሏል።

የኢትዮጵያ መንግስት የሱዳን ህዝቦች ጥበባዊ በሆነ መንገድ ችግሮቻቸውን በሰላማዊ ሁኔታ እንደሚፈቱም ያምናል ሲል ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው አመልክቷል።

እንደ ሁልጊዜው ሁሉ የኢትዮጵያ መንግስት ከሱዳን ዴሞክራሲያዊ ሂደት ስኬት ጎን ይቆማልም ሲል አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም