ቀጥታ፡

ወጣቱ የሽብር ቡድኑን እስከመጨረሻው በመታገል የሀገርን ህልውና ማስከበር አለበት

ደሴ፤ ጥቅምት 15/2014 (ኢዜአ ) ወጣቱ የህወሃት ወራሪ ቡድንን የመመከት ተግባሩን እስከ መጨረሻው የድል ቀን አጠናክሮ በመቀጠል የአካባቢውንም ሆነ የሀገርን ህልውና ሊያስከብር ይገባል ሲሉ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን አስገነዘቡ።

በዩኒቨርሲቲው የሰላም፤ ዲሞክራሲና ልማት ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር አልዩ ውዱ ለኢዜአ እንደገለጹት አሸባሪው የህወሓት ቡድን አገር ለማፍረስ የተቻለውን ጥረት ሁሉ እያደረገ ነው።

ከሰሞኑ ደሴና ኮምቦልቻን በወረራ ለመያዝ፣ ለመዝረፍና ለማውደም እንቅልፍ አጥቶ በየጫካው እየተሽሎከለከ መሆኑን አመልክተዋል።

ወጣቱ ከመከላከያ፣ ልዩ ኃይል፣ ፋኖና ሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የሽብር ቡድኑን ፊት ለፊት በጀግንነት እየተፋለመ መሆኑን አመልክተዋል።

"ወጣቱ የጀመረውን ትግል አጠናክሮ ከመቀጠል ውጭ መፈናቀል እንደማያዋጣው የተናገሩት ዶክተር አልዩ እስከመጨረሻው በመታገል የአባቶቹን የጀግንነት ታሪክ ማስቀጠል ይኖርበታል" ብለዋል፡፡

ወጣቱ ህብረተሰቡን በማስተባበር ያለ እረፍት አካባቢውን በመጠበቅና የሽብር ቡድኑን በመመከት የኢትዮጵያዊያንን ስነ ልቦና ከፍ ማድረግ እንዳለበት አስገንዘበዋል።

ሌላው በዩኒቨርሲቲው የፍልስፍና መምህር አቶ አደራጀው ዓለም በበኩላቸው "አሸባሪው ቡድን የኖረበትን የሀሰት የበሬ ወለደ ወሬ በመንዛት ህዝብ የማደናገር ሴራውን ቀጥሎበታል" ብለዋል።

የሽብር ቡድኑ ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር በመወገን በህብረተሰቡ ላይ የስነ ልቦና ጫና በማሳደር በቀላሉ ከተሞችን ተቆጣጥሮ ለመዝረፍና ለማውደም ጥረት አድርጓል'' ብለዋል።

ወጣቱ ተደራጅቶ የሽብር ቡድኑን መመከት በመቻሉ የጠላት እቅድ እንዳይሳካ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ለሰራዊቱ ደጀን በመሆን ስንቅና ትጥቅ ከማቀበል ባለፈ ፊት ለፊት ቡድኑን በመፋለም የጀመረውን መራር ትግል አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል።

"ወጣቱ ደሴና ኮምቦልቻን ላለማስደፈር በተደራጀ አግባብ የሚያደርገው ተጋድሎ የሚደነቅ፤ የጠላትን ስነ ልቦና የጎዳና ተስፋ ያስቆረጠ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል" ሲሉ አስገንዝበዋል።

የደሴ፣ የኮምቦልቻ፣ የሀርቡና የአካባቢዋ እንዲሁም ከሀገሪቱ ከተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ ወጣቶች የሽብር ቡድኑን ፊት ለፊት ለመፋለም ወደ ወሎ ግንባር እየዘመቱ መሆኑን ኢዜአ እየዘገበ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም