በአሸባሪው ህወሓት የሀሰት ወሬ የሚለቀቅ አካባቢም ሆነ የሚፈርስ ሀገር የለም - ኢዜአ አማርኛ
በአሸባሪው ህወሓት የሀሰት ወሬ የሚለቀቅ አካባቢም ሆነ የሚፈርስ ሀገር የለም
ጥቅምት 15/2014(ኢዜአ) "እኛ ኢትዮጵያውያን እያለን በአሸባሪው ህወሓት የሀሰት ወሬ የሚለቀቅ አካባቢም ሆነ የሚፈርስ ሀገር የለም" ሲል የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድንና የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ ተጫዋች ብርሃኑ ፈየራ ተናገረ።
የቀድሞው ፕሮፌሽናል ተጫዋች ብርሃኑ ፈየራ አሸባሪው የህወሃት ቡድን ኢትዮጵያን ለማፍረስ የፈጸመውን ወረራ ለመመከት በወሎ ግንባር ተሰልፏል፡፡
ብርሃኑ ፈየራ ትውልድና እድገቱ ደሴ ከተማ ሲሆን፤ በልጅነቱ ከእኩዮቹ ጋር በጨርቅ ኳስ ተጫውቶ አሳልፏል፡፡
የእግር ኳስ ክህሎቱን ወደ ፕሮፌሽናል ደረጃ በማሳደግም በኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን እና በቅዱስ ጊዮርጊስ የእግር ኳስ ክለብ ወርቃማ ጊዜያትን አሳልፏል፡፡
በተለይ ለቅዱስ ጊዮርጊስ የእግር ኳስ ክለብ ከ10 ዓመታት በላይ በመጫወት ከክለቡ የስኬት ታሪክ ጋር አብረው ከሚነሱ ተጫዋቾች መካከል ተጠቃሽ ነው፡፡
ብርሃኑ ፈየራ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አካባቢዎች ወረራ በመፈጸም በሰላማዊ ዜጎች ላይ ግፍ እየፈጸመ የሚገኘውን አሸባሪው የህወሃት ቡድንን ለመፋለም የክተት ጥሪውን ተቀላቅሎ ግንባር ላይ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ክህደት የፈጸሙባትን ኃይሎች በማጥፋት የምትታወቅ ሀገር መሆኗን ገልጾ፤ የኢትዮጵያ ጠላት የሆነውን አሸባሪው የህወሃት ቡድንን እስከ ህይወት መስዋዕትነት በመክፈል ለማፋለም ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል።
"እኛ ኢትዮጵያውያን እያለን በአሸባሪው ህወሓት የሀሰት ወሬ የሚለቀቅ አካባቢም ሆነ የሚፈርስ ሀገር የለም" ሲልም ነው የገለጸው፡፡
ወጣቶች ያለ መስዋትነት ነጻነት እንደማይገኝ በመገንዘብ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ግፍ እየፈጸመ ያለውን አሸባሪው የህወሃት ቡድንን በቁርጠኝነት መታገል እንዳለባቸው ተናግሯል፡፡
ኀብረተሰቡ አሸባሪ ቡድኑ በሚነዛው የሀሰት ወሬ ሳይደናገር ለመከላከያ ሰራዊቱ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርቧል፡፡
"አሸባሪ ቡድኑ በአጠረ ጊዜ ውስጥ ተደምስሶ ኢትዮጵያና ልጆቿ እፎይ የሚሉበት ጊዜ ሩቅ አይደለም" ሲልም ያለውን እምነተ ገልጿል፡፡