ኀብረተሰቡ በማህበራዊ ሚዲያ በሚለቀቁ ሀሰተኛ መረጃዎች ሳይደናገር ለህልውና ዘመቻው ስኬት የበኩሉን ድጋፍ ማድረግ አለበት - ኢዜአ አማርኛ
ኀብረተሰቡ በማህበራዊ ሚዲያ በሚለቀቁ ሀሰተኛ መረጃዎች ሳይደናገር ለህልውና ዘመቻው ስኬት የበኩሉን ድጋፍ ማድረግ አለበት
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14/2014(ኢዜአ) ኀብረተሰቡ በማህበራዊ ሚዲያ በሚለቀቁ ሀሰተኛ መረጃዎች ሳይደናገር ለህልውና ዘመቻው ስኬት የሚጠበቅበትን ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ግለሰቦች ገለጹ፡፡
በኢትዮጵያ የህልውና አደጋ በደቀነውን አሸባሪው ህወሓት ላይ እየተወሰደው ያለውን እርምጃ ተከትሎ ህዝቡን የሚያሳስቱ ሀሰተኛ መረጃዎች በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች እየተለቁቁ ይገኛሉ።
በማህበራዊ ሚዲያ የሚለቀቁ አብዛኛዎቹ ሀሰተኛ መረጃዎች በህዝቦች መካከል ያለውን አንድነት ለመሸርሸር ዓላማ ያደረጉ ቅስቀሳዎች ናቸው፡፡
አስተያየት ሰጪዎቹ ኀብረተሰቡ በማህበራዊ ሚዲያዎች በሚለቀቁ የሀሰተኛ መረጃዎች መደናገር እንደሌለበትና መረጃን ከትክክለኛ ምንጭ መውሰድ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
በማህበራዊ ሚዲያ የሚለቀቁ መረጃዎችን ትክክለኝነት ሳያረጋግጡ ለሌሎች ማጋራት ተገቢ አለመሆኑንም ነው ያነሱት፡፡
ዶክተር አስማማው ተገኝ በአሁኑ ወቅት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ሀሰተኛ መረጃዎች በስፋት እየተሰራጩ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ ኀብረተሰቡ መረጃን ከተዓማኒ ምንጮች ብቻ መውሰድ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚለቀቁ መረጃዎችን ከመጠቀማችን በፊት ማጣራት እንደሚገባ የገለጹት ደግሞ አቶ ሰለሞን አሰፋ ናቸው።
ወይዘሮ ጥሩወርቅ ተጫነ በበኩላቸው ኀብረተሰቡ አንድነቱን ከሚሸረሽሩት ጉዳዮች ራሱን ጠብቆ ለመከላከያ ሰራዊቱ ደጀን መሆኑን በተግባር ማሳየት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ህብረተሰቡ በአንድነት መቆም እንዳለበትም ነው ያነሱት፡፡
ወይዘሮ የኔወርቅ ዘገየ፤ ኀብረተሰቡ በማህበራዊ ሚዲያዎች በሚለቀቁ ሀሰተኛ መረጃዎች ሳይሸበር ለመከላከያ ሰራዊቱ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
ኀብረተሰቡ በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች በሚችለው ሁሉ ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አሸባሪው ህወሃት በማህበራዊ ሚዲያ የሀሰተኛ መረጃዎችን በማሰረጫት ኢትዮጵያውያንን ለመከፋፈል እየሰራ መሆኑ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡