ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እስካሁን 200 ሺህ ችግኞችን ለጎረቤት አገራት ለግሳለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እስካሁን 200 ሺህ ችግኞችን ለጎረቤት አገራት ለግሳለች
ጥቅምት 14/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እስካሁን 200 ሺህ ችግኞችን ለጎረቤት አገራት ማበርከቷን የአረንጓዴ አሻራ የቴክኒክ ኮሚቴ አስታወቀ።
በተጠናቀቀው ክረምት ”ኢትዮጵያን እናልብሳት” በሚል መሪ ሃሳብ 6 ቢሊዮን ችግኞችን የመትከል መርሃ ግብር ሲከናወን ለጎረቤት አገራት ደግሞ 1 ቢሊዮን ችግኞችን ተደራሽ የማድረግ እቅድ እንደነበር ይታወቃል።
በዚህም ኢትዮጵያ እስካሁን 200 ሺህ ችግኞችን ለተለያዩ ጎረቤት አገራት ማበርከቷን የአረንጓዴ አሻራ የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር አደፍርስ ወርቁ በተለይም ለኢዜአ ገልጸዋል።
በመርሃ ግብሩ ለኤርትራ 80 ሺህ፣ ለጅቡቲ 40 ሺህ እንዲሁም ለፑንት ላንድና ሶማሌላንድ እያንዳንዳቸው 40 ሺህ ችግኞች እንዲደርሷቸው ተደርጓል ብለዋል።
በቀጣይም ለሌሎች ጎረቤት አገራት ችግኞችን የማድረስ ስራ ይከናወናል ነው ያሉት ዶክተር አደፍርስ፡፡
በአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብር ኢትዮጵያ የአካባቢውን አገራትም አብሮ የማልማት እቅድ ይዛ እየሰራች ትገኛለች ብለዋል።
በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እስካሁን ያታዩ መልካም ውጤትና ተሞክሮዎችን በመቀመር ችገሮችን ለመፍታት የሚያስችል የዳሰሳ ጥናት ለማድረግ ታቅዷልም ነው ያሉት ዶክተር አደፍርስ፡፡
በዳሰሳው በ2013 ዓ.ም የተተከሉ ችግኞችን የፅድቀት መጠን የመለየት ስራ የሚከናወን ሲሆን በተያዘው ዓመት በዘርፉ የሚከናወነው ልማት ላይ ውይይት ይደረጋል ነው ያሉት።
በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በመጀመሪያውና ሁለተኛው ዙር በድምሩ 9 ቢሊዮን ችግኞች በኢትዮጵያ መተከሉን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር፤ የአካባቢ ብክለትና የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትላቸውን ችግሮች ለመፍታት ታስቦ እየተከናወነ መሆኑ ይታወቃል።