ቀጥታ፡

ኀብረተሰቡ በሀገሪቱ የተለያዪ አካባቢዎች በችግር ውስጥ ላሉ ዜጎች ድጋፍ እንዲያደርግ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ጥሪ አቀረበ

ጥቅምት 14/2014 (ኢዜአ) ኀብረተሰቡ በሀገሪቱ የተለያዪ አካባቢዎች በሰውሰራሽና ተፈጥሯዊ ችግሮች ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ድጋፍ እንዲያደርግ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ጥሪ አቀረበ፡፡
 ማህበሩ በሀገሪቱ የተለያዩ አከባቢዎች ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች እገዛ በማድረግ ላይ መሆኑንም ነው ያስታወቀው፡፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የሰብዓዊ ዲፕሎማሲና የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ዶክተር ሰለሞን አሊ ማህበሩ ሰውሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች የሚያሳድሩትን ተፅዕኖ መቋቋም የሚያስችል የድጋፍ ስራዎችን እያከናወነ  እንደሚገኝ ገልፀዋል ።

ለአብነትም ማህበሩ ባለፉት ሶስት ወራት በሰሜን ጎንደር ፣ ደቡብ ጎንደር ፣ በሰሜን ወሎና በደቡብ ወሎ አካባቢዎች በችግር ውስጥ ለሚገኙ ከ150 ሺህ በላይ ዜጎች ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል፡፡

ድጋፉም በዋናነት ምግብ-ነክ እና ምግብ-ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች፣ መድኃኒትና የአምቡላስ አገልግሎትን እንደሚያካትት ተናግረዋል፡፡

በደባርቅ፣  ጎንደር፣ ኮምቦልቻ፣ ደሴና ሀይቅ ለሚገኙ ሆስፒታሎች የመድኃኒት እገዛ ማድረጉንም ገልጸዋል ።

ማህበሩ በድርቅ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ድጋፍ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ነው ዶክተር ሰለሞን የተናገሩት፡፡

ማህበሩ ድጋፉን የሚያደርገው ከአባላት መዋጮ፣ በውጭ ሀገርና በሀገር ውስጥ ያሉ ተቋማትና ግለሰቦች ከሚያደርጉት ድጋፍ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ ኀብረተሰቡ በችግር ውስጥ ላሉ ወገኖቹ የሚጠበቅበትን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ከተመሰረተ ከ86 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ከ5 ሚሊዮን በላይ አባላትና ከ48 ሺህ በላይ በጎፈቃደኞች አሉት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም