ቀጥታ፡

ህወሀት በለኮሰው ጦርነት የተጎዳውን ሀገራዊ ምጣኔ ሀብት ለመደገፍ የመንግስት ወጪን መቀነስ ይገባል -ባለሙያዎች

ዲላ፣ ጥቅምት 14/2014 (ኢዜአ) ሽብርተኛው ህወሓት በለኮሰው ጦርነት የተጎዳውን የሀገር ምጣኔ ሀብት ለመደገፍ መንግስታዊ ወጪዎችን መቀነስ እንደሚገባ የዘርፉ ባለሙያዎች ገለጹ።
ባለሙያዎቹ በምግብ ሰብል እራስን ለመቻል የተጀመረው ጥረት በላቀ ትኩረት ሊመራ እንደሚገባም አመላክተዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ መካከል የሒሳብ ባለሙያው አቶ ተገኔ ጌታሁን እንዳሉት አሸባሪው ህወሓት በለኮሰው ጦርነት መንግስትና ህዝብ የህልውና ዘመቻ ውስጥ ገብተዋል።

ጦርነቱ እየተራዘመ መምጣቱን ተከትሎ ለህልውና ዘመቻው የሚውለው መዋዕለንዋይ በሀገሪቱ ምጣኔ ሃብት ላይ ጫና ማሳደሩ እንደማይቀር ተናግረዋል።

"ተገደን ወደ ጦርነት እንደገባን ሁሉ ጦርነቱና የውጭ ጫና የሚያስከትሉትን ፈተና ለመጋፍጥ መዘጋጀትና ሌሎች ያልተገቡ መንግስታዊ ወጪዎችን መቀነስ ይገባል" ብለዋል።

በሀገሪቱ ሜጋ ፕሮጀክቶችንና የመሰረተ ልማት ሥራዎችን ለማጠናቀቅ ከተቀመጠለት ጊዜ በፊት በጥራት የመጨረስ አቅምን ማሳደግ እንደሚገባም ባለሙያው ተናግረዋል።  

ይህም በተራዘመ መጠን የሚፈጠር የዋጋ ጭማሪን ለማስቀረት እንደሚያስችል ነው የገለጹት።

"የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ ወደ ሥራ እንዲገባ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ማሳደግና ማጠናከር ይገባል" ሲሉም አቶ ተገኔ አክለዋል።

"የዜጎችን የመግዛት አቅም ውስንነትና የተጋነነ የዋጋ ንረት ችግርን ለመፍታት ከሳይንሳዊ መፍትሄ በተጨማሪ የፖለቲካ ውሰኔን ይሻል" ያሉት ደግሞ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብት መምህር ዶክተር ታምራት ታደሰ ናቸው።

በጦርነት የተዳከመውን የሀገር ምጣኔ ሀበት ለመታደግ መንግስታዊ ወጪዎችን ከመቀነስ ባለፈ በምግብ ሰብል ራስን ለመቻል የሚከናወነው ሥራ በላቀ ትኩረት ሊመራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

"ዜጎችም ለሀገር ኢኮኖሚ ትርጉም ያለው አስተዋጾ ከማበርከት ባለፈ ሌቦች ሲሰርቁ ችላ ብሎ ከማለፍ ይልቅ ፊት ለፊት ማጋለጥና መቃወም ይገባል" ብለዋል።

ባለሃብቱና በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊም  የውጪ ምንዛሬ አቅምን ለማጎልበት በህጋዊ መንገድ በመስራት ለሀገራቸው ቅድሚያ የሚሰጡበት ጊዜው አሁን መሆኑን ተናግረዋል።

የጌዴኦ ዞን ሳይንስና ቴክኖሎጂ መምሪያ ሃላፊና የምጣኔ ሃብት ባለሙያ አቶ አብነት አክሊሉ በበኩላቸው "የሕዳሴው ግድብ ወደ ሃይል ማመንጨት ለመሸጋገር መቃረቡ ለተጎዳው ምጣኔ ሃብታችን የሚኖረው ፋይዳ የላቅ ነው" ብለዋል።

አቶ አብነት እንዳሉት ሀገራዊ አቅምን በማስተባበር የሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክትን ጨምሮ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን በማፋጠን ለሀገር ኢኮኖሚ አስተዋጽኦ እንዲኖራቸው ማድረግ ይገባል።

የቅንጦት እና የማይገቡ መንግስታዊ ወጪዎችን በመቀነስ የውጪ ምንዛሬ አቅምን ለማሳደግ መረባረብ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም