ደሴን የሚረግጣት የአሸባሪው ምርኮኛ ብቻ ነው፤ ከተማችንን አሳልፈን አንሰጥም---የደሴ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ደሴን የሚረግጣት የአሸባሪው ምርኮኛ ብቻ ነው፤ ከተማችንን አሳልፈን አንሰጥም---የደሴ ከተማ ነዋሪዎች
ደሴ (ኢዜአ) ጥቅምት 14/2014 የአሸባሪው የህወሓት ቡድን ምርኮኛ ካልሆነ በቀር ቡድኑ ደሴ ከተማን አይረግጥም፤ ከተማችንንም ለወራሪው አሳልፈን አንሰጥም ሲሉ የደሴ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
ነዋሪዎቹ ለመከላከያ ሠራዊቱ ግንባር ድረስ በመሄድ ስንቅና ትጥቅ በማቀበል ያላቸውን ደጀንነት በተግባር እያሳዩ ነው፡፡
ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ተክለጊወርጊስ ስኑ ለኢዜአ እንዳሉት አሸባሪው የህወሓት ቡድን ኢትዮጵያን ለማፍረስ የጀመረውን የጥፋት ተግባር አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
"የደሴ ከተማ ነዋሪዎችም አንድነታቸውን በማጠናከር ለመከላከያ፣ ለክልል ልዩ ኃይል እና ለፀጥታ አባላት ደጀን ሆነው ስንቅና ትጥቅ እያቀበሉ ይገኛሉ" ብለዋል፡፡
"ወራሪው የሽብር ቡድኑ በተለመደው የሀሰት ወሬ 'ደሴ ላይ በርካታ ሠራዊት አስገብተናል፤ ከተማዋን ተቆጣጥረናል' ቢልም በተባበረ ክንድ ሴራውን በማክሸፍ የእለት ተዕለት እንቅስቃሴያችንን ቀጥለናል" ሲሉም ተናግረዋል።
ደሴ ከተማን ላለማስደፈር ከአመራሩ ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ተክለጊወርስ "የአሸባሪው የህወሓት ቡድን ምርኮኛ ካልሆነ በቀር ቡድኑ ደሴ ከተማን አይረግጥም" ብለዋል።
"እኛ በህይወት እያለን ደሴ የአሸባሪው የህወሓት ቡድን መፈንጫ አትሆንም'' ያለው ደግሞ ወጣት አንዋር እንድሪስ የተባለ የከተማዋ ነዋሪ ነው፡፡
አንድነታቸውን በመጠበቅ ለሠራዊቱ ደጀን ከመሆን ባለፈ ፊት ለፊት ቡድኑን እየተፋለሙ መሆኑን ተናግሯል።
"እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ከፍለንም ቢሆን ነጻነታችንን በደማችን እንጠብቃለን፤ ከተማችንንም ለወራሪ ቡድን አሳልፈን አንሰጥም" ሲልም ወጣቱ ገልጿል።
የሀገር ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የኢትዮጵያ ህዝብ ከጫፍ እስከ ጫፍ በአንድነት መነሳቱ ብርታትና ወኔ እንደሆናቸው የገለጸው ወጣቱ፣ አካባቢያቸውን በንቃት ከመጠበቅ ባለፈ ወደ ከተማዋ ሰርጎ በመግባት የውሸት ሽብር የነዙ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር እንዲውሉ እያደረጉ መሆናቸውን ተናግሯል።
በወሎ ግንባር ለሰራዊቱ ስቅና ትጥቅ ማቀበሉን የገለጸው ወጣት አንዋር የከተማዋ ነዋሪዎች በተለይ ወጣቱ በወሬ ከተማዋን ለቆ ከመሸሽ ከሠራዊቱ ጎን ተሰልፎ ደህንነቱን እንዲያስጠበቅ መክሯል።
የደሴ ከተማ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ምሳየ ከድር በበኩላቸው የህብረተሰቡ ሁለተናዊ ተሳትፎ የሚደነቅና እስከ ድል ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።
የከተማ አስተዳደሩና ነዋሪ ከሠራዊቱና ከአመራሩ ጋር ያለው ቅንጅትና ቁርኝት ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን ጠቁመው በሁሉም ግንባሮች የተጀመረው ስንቅና ትጥቅ የማቀበል ዘመቻ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አስተዳደሩ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን አመልክተዋል።
"የህወሓት የሽብር ቡድን ደሴ ከተማን ይዠዋለሁ፤ አገልግሎት መስጫ ተቋማትም ተዘግተው ህዝቡ እየተፈናቀለ ነው" ብሎ የነዛው ወሬ ከእውነት የራቀ መሆኑን ገልጸዋል።
ህብረተሰቡ ለሰራዊቱ ደጀን ከመሆን ባለፈ የእለት ተእለት እንቅስቃሴውን ተረጋግቶ እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኢዜአ ሪፖርተር በደሴ ከተማ ተዘዋውሮ እንደተመለከተው ህብረተሰቡ የዕለት ተዕለት ሰላማዊ እንቅስቃሴውን የቀጠለ ሲሆን የደጀንነት ስራውንም ጎን ለጎን እያከናወነ መሆኑን ማረጋገጥ ችሏል፡፡