የአየር ጥቃቱን በተመለከተ አንዳንድ ሚዲያዎች አሸባሪው ህወሃት የሚያሰማውን የውሸት ጩኸት እየደገሙ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአየር ጥቃቱን በተመለከተ አንዳንድ ሚዲያዎች አሸባሪው ህወሃት የሚያሰማውን የውሸት ጩኸት እየደገሙ ነው
ጥቅምት 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአየር ጥቃቱን በተመለከተ አንዳንድ ሚዲያዎች አሸባሪው ህወሃት ‘ንጹሃን ሰዎችና የትምህርት ተቋማት ተደበደቡ’ በሚል የሚያሰማውን የውሸት ጩኸት እየደገሙ እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
የኢፌዴሪ አየር ሃይል በትግራይ ክልል በመቀሌ ከተማ የሚገኘውን የአሸባሪው ህወሃት ቡድን የወታደራዊ ማሰልጠኛና ማዘዣ ማእከል የሆነውና የቀድሞ የአገር መከላከያ ሰራዊት ማሰልጠኛ የነበረውን ቦታ ከትናንት በስቲያ በአየር መደብደቡ ይታወቃል።
በዕለቱ የኢትዮጵያ መንግስት ፈቃድ የሰጣቸው ሁለት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የእርዳታ አቅራቢ አውሮፕላኖች በመቀሌ ማረፍ እንደማይችሉ በአካባቢው የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ተነግሯቸው ወደ አዲስ አበባ በመመለስ አርፈዋል።
የተመድ ቃል አቀባይ ስቴፋኒ ዱጃሪክ እንደገለጹት፤ አውሮፕላኖቹ በመንግስት ፈቃድ ቢያገኙም በመቀሌ ተቆጣጣሪዎች እንዳያርፉ ተነግሯቸው እንዲመለሱ ተደርጓል።ይህ ሆኖ ሳለ ግን አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን እውነታውን በመሳት አውሮፕላኖቹ በመቀሌ እንዳያርፉ የተደረገው በሚፈጸመው የአየር ጥቃት እንደሆነ በመግለጽ እየዘገቡ እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።
ሚኒስቴሩ ትናንት ምሽት ላይ ባወጣው መግለጫ ሚዲያዎቹ አሸባሪው ህወሃት የአየር ድብደባውን በተመለከተ ‘ንጹሃን ሰዎችና የትምህርት ተቋማት ተደበደቡ’ በሚል የሚያሰማውን የውሸት ጩኸት እየደገሙ እንደሆነ አስገንዝቧል።
የኢፌዴሪ አየር ሃይል የአየር ጥቃቱን እየፈጸመ የሚገኘው እጅግ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ በተመረጡ ኢላማዎች ላይ መሆኑን የገለጸው ሚኒስቴሩ፤ የአሸባሪው ቡድን ወታደራዊ ማዘዣ እና ማሰልጠኛዎች ብቻ የጥቃቱ ኢላማ መሆናቸውን ገልጿል።