ቀጥታ፡

የእርዳታ አውሮፕላኖች ከመቀሌ የተመለሱት በስፍራው በሚገኙ የበረራ ተቆጣጣሪዎች ፈቃድ በመከልከላቸው ነው

ጥቅምት13/ 2014 (ኢዜአ) በትናንትናው ዕለት የእርዳታ አውሮፕላኖች ከመቀሌ ሳያርፉ የተመለሱት በአየር ጥቃቱ ሳቢያ ሳይሆን በስፍራው በሚገኙ የበረራ ተቆጣጣሪዎች ፈቃድ በመከልከላቸው መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ጉዳዩን አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል።

አገልግሎቱ በመግለጫው ትናንት የኢፌዲሪ አየር ሃይል በመቀሌ የአሸባሪው ህወሃት ቡድን የወታደራዊ ማሰልጠኛና ማዘዣ ማእከል የሆነውና የቀድሞ የመከላከያ ሰራዊት ማሰልጠኛ የነበረውን ቦታ በአየር መደብደቡን አስታውሷል፡፡

በዚሁ ዕለት ከኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት በኩል ፈቃድ የተሰጣቸው ሁለት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የእርዳታ አውሮፕላኖች በመቀሌ እንዲያርፉ በስፍራው ካሉ የበረራ ተቆጣጣሪዎች ፍቃድ በመከልከላቸው ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸውንም ጠቁሟል፡፡

መግለጫው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፈን ዱጃሪክ አውሮፕላኖቹ ከፌደራል መንግስት ፈቃድ የተሰጣቸው እንደሆኑና ወደ አዲስ አበባ የተመለሱት በኤርፖርቱ የበረራ ተቆጣጣሪዎች ፍቃድ በመከልከላቸው ብቻ መሆኑንም አሳውቀዋል ነው ያለው።

ይሁን እንጂ እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ አንዳንድ የውጭ መገናኛ ብዙሃን የእርዳታ አውሮፕላኖቹ የተመለሱት በየአየር ጥቃቱ ሳቢያ እንደሆነ በማስመሰል የተሳሳተ ዘገባ ማሰራጨታቸውን ጠቅሷል፡፡

የአየር ጥቃቶቹ በከፍተኛ ጥንቃቄ የተወሰዱና የሽብር ቡድኑ ለእኩይ አላማ የሚጠቀምባቸውን የመገናኛና የወታደራዊ ማሰልጠኛዎችን ብቻ ኢላማ ያደረጉ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡

የሽብር ቡድኑ ይህንን መሰል የተሳሳቱ መረጃዎችን በማውጣት ህብረተሰቡን በሃሰተኛ ምስሎች ለማወናበድ የሚወስዳቸውን እርምጃዎች ተገንዝቦ ጥንቃቄን መውሰድ እንዳለበትም የመንግስት የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ጥሪውን አቅርቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም